ካፒታል ሆቴል እና ሆሴዕ ሪል እስቴት በመቄዶንያ የአረጋውያን እና የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል በአካል በመገኘት ከፍተኛ ድጋፍ አድርገዋል።
በዚሁ መሠረት ካፒታል ሆቴል 1.5 ሚሊዮን ብር የሚገመት ቁሳቁስና አልባሳት እንዲሁም የ1 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፣ የዘወትር አጋራቸው የሆነው ሆሴዕ ሪል እስቴትም የ2 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ አበርክቷል።
ሆሴዕ ሪል እስቴት ዘመናዊ ቤቶችንና ሕንፃዎችን ገንብቶ ከማስረከብ ባለፈ፣ የተሰበረውን የሰዎችን ሕይወት በመጠገን እና የሰብአዊነት ግዴታውን በመወጣት ረገድ አርአያነት ያለው ተግባር ፈጽሟል።
ተቋማቱ ይህንን ድጋፍ ሲያደርጉ የመጀመሪያቸው አለመሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ላለፉት ጊዜያትም የማዕከሉ የቅርብ አጋር በመሆን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሲረዱ ቆይተዋል።
ሁለቱም ተቋማት መስከረም 29 ቀንን በስማቸው በመሰየም የተጀመረው አጋርነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና አረጋውያኑ በሚፈልጉት በማንኛውም ጊዜ ከጎናቸው ለመቆም ቃል ገብተዋል።
የመቄዶንያ መስራች ዶ/ር ቢንያም በለጠ በበኩላቸው ለካፒታል ሆቴል ባለቤት (አቶ የማነህ) እና ለካፒታል ሆቴል ሰራተኞች፣ ለሆሴዕ ሪል እስቴት የቦርድ አባላት እና ሰራተኞች፣ ጥሪ ተደርጎላቸው ለተገኙ የሚዲያ አካላት፣ ጋዜጠኞች እንዲሁም ታላላቅ እንግዶች በመቄዶንያ አረጋዉያን እናቶች እና አባቶች ስም ምስጋና አቅርበዋል።
ምንጭ፦ መቄዶንያ-mekedonia


















