6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በ4ኛ ዓመት የስራ ዘመኑ ባካሄደው 9ኛ መደበኛ ስብሰባው የሪል እስቴት ልማት እና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አፅድቋል።
የተከበሩ እሸቱ ተመስገን (ዶ/ር) የሪል እስቴት ልማት እና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ የተዘጋጀውን ሪፖርትና የውሳኔ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
የሪል እስቴት ልማቱ አቅርቦት እጅግ ወደኋላ የቀረና የህዝቡን ፍላጎት የማያሟላ በመሆኑ፣ የማይንቀሳቀስ ንብረት ግመታ ስርዓቱ ዘመናዊና በመረጃ በተደገፈ መልኩ ተገማች ዋጋ እንዲኖረው ማድረግ በማስፈለጉ እና በማይንቀሳቀስ ንብረት ገበያው ግልጽነት መጓደሉ የኢኮኖሚ መዛባት እያስከተለና የመንግስትን ጥቅም የሚያሳጣ እንዳይሆን ለማድረግ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ረቂቅ አዋጁ፤ አዋጅ ቁጥር 1357/2017 ሆኖ በሁለት ተቃውሞና በአንድ ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ፀድቋል፡፡
የሪል እስቴት ልማት እና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተደረጉ ማሻሻያዎች መካከል ጥቂቶቹ :-
- “ሪል ስቴት” የሚለው ቃል “ሪል እስቴት” በሚል ተተክቷል
- የሪል እስቴት፣ ሪል እስቴት ልማትና ሪል እስቴት አልሚን ጨምሮ ሌሎች ቃላት ትርጉም ላይ ማሻሻያ ተደርጓል
- የሪል እስቴት አልሚ ለመባል 50ቤቶች መገንባትን ይጠይቅ የነበረው መለኪያውን ከቤቶች ቁጥር ይልቅ ጠቅላላ የግንባታ ስፋትን በማድረግ ጠቅላላ የግንባታ ስፋት ከ1500ካሬሜ በላይ በሚል ተስተካክሏል
- ለአልሚዎች ማበረታቻ የሚደረግበት የቤት ቁጥር 500 ፣ 1000 እና 5000 በላይ የነበረውን በግማሽ በማሻሻል 250 500 እና 2500 ተደርጓል
- ከ80% በላይ ግንባታ ሳያጠናቅቁ ቤት ስም ማዞርን ይከለክል የነበረው ላይ ቤቶችን ለማስረከብ መሰረታዊ የመገልገያ መሰረተ ልማቶችን ማሟላት እንዳለበት ተካቷል። ይህም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎችን፣ አሳንሰር፣ የውሃ መስመር ዝርጋታና የሳኒተሪ ስራዎች ፣ መብራትን ያካተተ ነው።
- የመኖሪያ ቤት ገዢዎች ማህበር ማቋቋምን አስገዳጅ አድርጎት የነበረው የመኖሪያ ቤቶች ባለቤቶች ማህበር በሚል ተክቶታል
- የሪል እስቴት ግብይት ክፍያዎች በባንክና በሌሎች የኤሌክትሮኒክስ ዘዴ መተላለፍ እንዳለባቸውና ገዢም ሆነ ሻጭ መረጃዎቻቸውን ሰንደው መያዝ እንዳለባቸው ተገልጿል
- በቅድመ ሽያጭ ግንይት ለመሰማራት የሪል እስቴት አልሚዎች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታቸውን ማሳገድ እንዳለባቸው ይገልጽ የነበረው እንዲቀር ተደርጓል። ዋስትና የሚሰጥበት አሰራር በቀጣይ በሚወጡ የአሰራር መመሪያዎች ይገለጻል ተብሏል ይህም አልሚዎች በተወሰነ ደረጃ ፕሮጀክቶቻቸውን ለመደገፍ ብድር እንዲያገኙ ላለመከልከል ነው።
- በዘርፉ ለአልሚዎች የሚደረጉ ማበረታቻዎች በደንብ እንደሚወሰን ተገልጿል
- የማይንቀሳቀስ ንብረት ግመታ በገበያ ንጽጽር መሰረት እንደሚወሰን ነገር ግን እንደ ግመታው ዓላማ በመተኪያ ወጪ ወይም ገቢን ወደ ካፒታል በመቀየር ሊሰራ ይችላል ተብሏል
- የማይንቀሳቀስ ንብረት ገማች የታደሰ የሙያ ፈቃድ ሊኖረው እንደሚገባ
- በግብይት ውስጥ “እንደራሴ”ና “ደላላ” በሚል የተጠቀሱት ከዘርፉ ጋር የማይሄድ በመሆኑ ” አገበያይ” በሚል ተተክቷል
- በአገበያይነትና በህንጻ አስተዳዳሪነት የሚሳተፍ አካል ተፈላጊው የትምህርት ዝግጅትና የሙያ ስነምግባር ያሟላ መሆን እንዳለበት ተገልጿል።


















