በተያዘው 2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ለመግስታዊ ተቋማት ግንባታ እና ማስፋፊያ 551.96 ሄክታር የለማ መሬት ተዘጋጅቶ ውል የማሰር ስራ እየተከናወነ መሆኑን በመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የለማ መሬት ማስተላለፍ እና ሊዝ ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘሪሁን ቢቂላ ተናግረዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ ከ17 የፌደራል፣ የከተማ አስተዳደርና የክልል መንግስታት ዘንድ የቀረበ የቦታ ይሰጠን ጥያቄ በቢሮው ስትራቴጂክ ካውንስል አባላት ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ በጥያቄያቸው መሰረት ለመንግስት ተቋማት ግንባታና ማስፋፊያ 533.28 ሄክታር፣ ለስራ እድል ፈጠራ 7.65 ሄክታር እንዲሁም ለፌደራል እና የክልል መንግስታት 59.061 ካሬ ሜትር የለማ መሬት ተዘጋጅቶ ከሊዝ ክፍያ ነፃ እየተላለፈ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
አክለውም በበጀት ዓመቱ የመሬት ሊዝ ጨረታን ጨምሮ ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች የሚውል 587.46 ሄክታር መሬት ለማዘጋጀት መታቀዱን አስታውሰው በመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብቻ መንግስታዊ ተቋማትን ጨምሮ 672.57 ሄክታር የለማ መሬት በማዘጋጀት ከወዲሁ የበጀት ዓመቱን እቅድ ማሳካት መቻሉን አብራርተዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ቢሮው በቅርቡ ባወጣው 6ኛ ዙር የመሬት ሊዝ ጨረታ 132 ፕሎቶችን ለውድድር አቅርቦ ከጨረታው አሸናፊዎች ከወዲሁ 1.176 ቢሊየን ብር መገኘቱን ገልፀው ውል የማሰሩ ስራ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ 1.8 ቢሊየን ብር ለማግኘት እየተሰራ ስለመሆኑም የለማ መሬት ማስተላለፍ እና ሊዝ ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ዘሪሁን ቢቂላ ጨምረው ተናግረዋል፡፡
ከጨረታ ሂደቱ ጋር ተያይዞም ሆን ብለው የማጭበርበር ወንጀል ሙከራ ያደረጉ 16 ተጫራቾች CPO እንዲወረስና በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለቢሮው የውሳኔ ሀሳብ መቅረቡን አንስተው በቀጣይ ተጫራቾች ከህገ ወጥ ተግባራት እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡


















