“ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ የከፈልንበትን አፓርታማዎቻችንን አስረክበን” በሚል ስድስት ቤት ገዢዎች ኖህ ሪል እስቴትን ወደ ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወስደውታል።
ገዢዎቹ ክስ የመሰረቱበት በአዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ሴቶች አደባባይ አካባቢ በሚገኘው ባለ 19 ወለል ኖህ ቪክትሪ ሳይት ነው።
ከሳሾቹ እንደገለጹት፣ አልሚው ኖህ ሪል እስቴት በ36 ወራት ውስጥ ግንባታውን አጠናቆ አፓርታማዎቹን ሊያስረክብ ውል ቢገባም፣ በተግባር ግን ስድስት ዓመታት እንደፈጀበት ገልጸዋል።
ከሳሾቹ እንደሚሉት፣ ኖህ ሪል እስቴት የአፓርትመንት መኖሪያ ቤቶቹን ከውሉ ቀን ጀምሮ በሦስት ዓመታት ውስጥ አጠናቆ ሊያስረክባቸው ውል ቢገባም፣ “በዚህ ጊዜ ውስጥ ተከሳሽ ለከሳሾች አፓርትመንቱን አጠናቆ ማስረከብ አልቻለም” ብለዋል።
ግንባታው የተጠናቀቀው በዚህ ዓመት ከሦስት ወራት በፊት መሆኑን ጠቅሰው፣ ከረጅም ጊዜ መዘግየት በኋላም ቢሆን በውሉ መሠረት ለከሳሾች ለማስረከብ ፈቃደኛ እንዳልሆነ አስረድተዋል።
በዚህ ምክንያት መጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም. በጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ቢሰጡም፣ አዎንታዊ ምላሽ ባለመሰጠቱ ወደ ፍርድ ቤት ለመሄድ እንደተገደዱ በክሳቸው ገልጸዋል።
ኖህ ሪል እስቴት በበኩሉ፣ ከሳሾቹ የተናጠል ካርታ በተዘጋጀበት ወቅት የተፈጠረውን የካሬ ልዩነት ክፍያ አልከፈሉም ብሏል። በጉዳዩ ዙሪያ ከገዢዎቹ ጋር ቢወያይም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መወሰዳቸውን ገልጿል።
የሁለቱ ወገኖች ልዩነት የተፈጠረው ኖህ ሪል እስቴት “ቤታችሁ ተጠናቋል” ብሎ ከገለጸ በኋላ ቁልፍ ለመረከብ የቀረቡትን ገዢዎች፣ “ክፍለ ከተማው የተናጠል ካርታ ሲያዘጋጅ የካሬ ልዩነት ተፈጥሯል፤ ተጨማሪ ክፍያ ክፈሉ” በማለቱ መሆኑን ገዢዎቹ ገልጸዋል።
የክፍያ ጭማሪውም የመጣው በተናጠል ካርታ ሲዘጋጅ የጋራ መጠቀሚያ ቦታዎች ካሬ በመጨመሩ መሆኑን አስረድተዋል።
ኖህ ሪል እስቴት፣ በውሉ የተጠቀሰው ካሬ ስፋት ከ10 በመቶ በላይ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቅሶ፣ በውሉ መሠረት ተጨማሪ ክፍያ ለመጠየቅ መብት እንዳለው ገልጿል።
የክሱ ሰነድ እንደሚያሳየው፣ 1ኛው ከሳሽ አቶ ታምራት ገዛኸኝ ጌሮ 176.74 ካሬ ሜትር ንፁህ ስፋት፣ 31.24 ካሬ ሜትር የጋራ መጠቀሚያና መዘዋወሪያ በድምሩ 207.98 ካሬ ሜትር የሚሆን መኖሪያ ቤት በ12 ሚሊዮን ብር ገዝተው ክፍያቸውን አጠናቀዋል።
ሌሎች ከሳሾችም በተመሳሳይ የቤታቸውን፣ የጋራ ቦታና የመዘዋወሪያ ስፋት በመግለጽ ክፍያቸውን ሙሉ በሙሉ እንዳጠናቀቁ የክስ ሰነዱ ያስረዳል።
ኖህ ሪል እስቴት ለፍርድ ቤት በሰጠው ምላሽ ከሳሾቹ ክፍያቸውን መፈጸማቸውንና ግንባታው መጠናቀቁን አምኖ፣ ነገር ግን የተናጠል ካርታ ሲዘጋጅ ከ10 በመቶ በላይ የካሬ ጭማሪ መታየቱን ጠቅሷል።
ለአብነት፣ 1ኛው ከሳሽ በውሉ 207.98 ካሬ ሜትር የተገለጸው የቤት ስፋት በተናጠል ካርታ 265 ካሬ ሜትር ሆኖ መገኘቱን ገልጿል።
2ኛና 3ኛ ከሳሾችም 207.98 ካሬ ሜትር በውል ተገልጾ በካርታ 265.11 ካሬ ሜትር መሆኑን፣ ይህም 57.13 ካሬ ሜትር ጭማሪ መሆኑን አመልክቷል።
4ኛው ከሳሽም ተመሳሳይ 57.13 ካሬ ሜትር ጭማሪ እንዳለበት፣ ቀሪዎቹ ሁለት ከሳሾች ደግሞ 44.5 ካሬ ሜትር ልዩነት እንዳሳዩ ሰነዱ ያመለክታል።
ከሳሾቹ በበኩላቸው፣ በአፓርታማዎቻቸው ላይ ምንም ተጨማሪ የካሬ ስፋት እንዳልተጨመረ ገልጸው፣ በተናጠል ካርታ ተጨመረ ተብሎ የተጠየቀው ከ3 እስከ 4 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ተጨማሪ ክፍያ ” አይመለከተንም ” በሚል አንከፍልም ብለዋል።
በተጨማሪም፣ በውላቸው አንቀጽ 6.1 መሠረት የአፓርትመንቱ የሽያጭ ዋጋ ላይ ምንም ዓይነት ማስተካከያ እንደማይደረግ ተስማምተው እንደነበር ጠቅሰዋል።
እንዲሁም በውሉ አንቀጽ 8.5 መሠረት ተከሳሹ ለእያንዳንዱ ገዢ የጋራ መጠቀሚያዎችን ሳይጨምር ንፁህ ስፋቱን የሚያሳይ ነጠላ ካርታ ማዘጋጀት ግዴታው እንደሆነ ገልጸዋል።
ኖህ ሪል እስቴት በምላሹ “ተከሳሽ በራሱ ካርታ የማዘጋጀት ስልጣን የለውም” ሲል ገልጿል።
በተጨማሪም ኖህ ሪል እስቴት፣ በውሉ አንቀጽ 13 መሠረት በአፓርትመንቱ ስፋት ላይ እስከ10 በመቶ ድረስ የመጨመር ወይም የመቀነስ ሁኔታ ካለ ሁለቱም ወገኖች በውሉ የተጠቀሰውን ልኬት ለመቀበል እንደተስማሙ ጠቅሶ፣ ከሳሾቹ የካሬ ልዩነቱን ሳይከፍሉ ቤት እንረከብ ማለታቸው “በተከሳሽ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ የውል ጥሰት” መሆኑን ገልጾ፣ ያቀረቡት ክስ ተቀባይነት እንደሌለው አስረድቷል።
ባለፈው ሰኔ 29 ጉዳዩን የተመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት፣ ኖህ ሪል እስቴት ተጨማሪ የሰነድ ማስረጃ አያይዞ እንዲያቀርብ የጠየቀውን ጥያቄ በመፍቀድ ጉዳዩን ለጥቅምት 10 ቀን 2019 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ምንጭ: ቲክቫህ ኢትዮጵያ


















