ሮክስቶን ኢትዮጵያ፣ አርቲስት አምለሰት ሙጬን የከፍታ አፓርትመንቶች ብራንድ አምባሳደር አድርጎ መረጣት።
የጀርመኑ ሪል እስቴት ሮክስቶን ኢትዮጵያ፤ ታዋቂዋን ተዋናይት፣ የሚዲያ ባለሞያና ግንባር ቀደም የአረንጓዴ ልማት ተሟጋች አርቲስት አምለሰት ሙጬን፣ የከፍታ አፓርትመንቶች ብራንድ አምባሳደር አድርጎ መሾሙን በዛሬው ዕለት ይፋ አደረገ፡፡
የዛሬ አራት ዓመት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ወደ ሪል እስቴት ኢንቨስትመንት የገባው ሮክስቶን ኢትዮጵያ፤ በመዲናዋ ሲግናል አካባቢ በ1 ቢሊዮን ብር በጀት ከፍታ በአዲስ አበባ የተሰኘ የመኖሪያ አፓርትመንት ግንባታ የጀመረ ሲሆን መኖሪያ ቤቶቹ ከ30 ሚሊዮን ብር እስከ 150 ሚሊዮን ብር ያወጣሉ ተብሏል፡፡

አርቲስት አምለሰት ሙጬ የከፍታ አፓርትመንቶች አምባሳደር ሆና መመረጧን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት ጠዋት ረፋዱ ላይ በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል የሮክስቶን ኢትዮጵያ ከፍተኛ አመራሮችና አርቲስቷ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡ ሲሆን፤ የፊርማ ሥነስርዓትም ተከናውኗል፡፡
አርቲስት አምለሰት ሙጬ በብራንድ አምባሳደርነት የተመረጠችበት ዋነኛው ምክንያት አረንጓዴ ዓለምን ለመፍጠር በሚደረጉ ሁለንተናዊ ተሳትፎዎች ላይ እውቅናዋን ተጠቅማ የተለያዩ ንቅናቄዎችን ማሳካት በመቻሏ ነው ያለው ሮክስቶን ሪል እስቴት፤ ከዚህ በተጨማሪም አርቲስቷ ያላት ሰብዕና፣ ቁርጠኝነትና ትልልቅ ራዕዮቿ በሙሉ ድምፅ እንድትመረጥ አድርገዋታል ብሏል።
አርቲስት አምለሰት አምባሳደር ሆና በመመረጧ የተሰማትን ስሜት ስትገልፅ፤ “ዘላቂነት ካለው የሪል እስቴት ልማት ኩባንያ ጋር አብሬ በመስራቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። ከፍታ፤ አዲስ አበባን የሚያምር ገፅታ በማላበስ፣ አረንጓዴነቷን በማስቀጠል የተፈጥሮ ሀብትን ለትውልድ እያስቀጠለ የሚገኝ ፕሮጀክት ነው። በተጨማሪም እኔ እራሴ በከፍታ አፓርትመንት የቤት ባለቤት በመሆኔ ሁሌም ኩራት ይሰማኛል፡፡” ብላለች፡፡

ከኩባንያው ጋር ለመሥራት የተስማማሁት ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑና በህንጻዎቹ ዲዛይን ላይ የኢትዮጵያን ባህልና ታሪክ በማንጸባረቁ ነው ብላለች – አርቲስት አምለሰት፡፡
የሮክስቶን መሥራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚው ሚስተር ዲትሪክ ኢ. ሮጄ ስለ አምለሰት በብራንድ አምባሳደርነት መመረጥ ሲናገሩ፤ “አርቲስት አምለስት ባላት የግል ማንነት ከፍታ የያዘውን የዘመናዊነትና የአካባቢ ጥበቃ ተነሳሽነት ለብዙ ደንበኞቻችን ለማሳየት ወሳኝና ተመራጭ እንስት ናት። በአስገራሚ ሰብዕናዋና ከማህበረሰቡ ጋር ባላት ጠንካራ ትስስር፣ ተፅዕኖ የመፍጠር አቅሟ ከፍተኛ ስለሆነ ከፍታ አፓርትመንቶችን በማስተዋወቅ እንዲሁም አዲስ ነገሮችን በጋራ የመፍጠር ራዕያችንን ታሳካለች ብለን እናምናለን፡፡” ብለዋል፡፡
የሮክስቶን ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አድያምሰገድ ኢያሱ በበኩላቸው፤ “አርቲስት አምለሰት ሙጬ ብራንድ አምባሳደራችን በመሆኗ በጣም ደስተኞች ነን። አምለሰት የእኛን የልህቀት፣ የጥራትና የማህበራዊ ሀላፊነት እሴቶች የምትጋራ መልካም ሰብዕና ያላት ድንቅ አርቲስት ናት። ለድርጅታችን ትልቅ ሀብት እንደምትሆንና ወደምንፈልጋቸው ደንበኞቻችን እንዲሁም ባለድርሻ አካላት እንድንደርስ ትረዳናለች ብለን እናምናለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሮክስቶን ሪል እስቴት በጀርመን የተመሰረተ በግንባታው ዘርፍ ሙሉ አገልግሎት የሚሰጥ የሪል እስቴት ገንቢና የኢንቨስትመንት ድርጅት ሲሆን፤ በጀርመን፣ ስፔንና ፖርቹጋል ውስጥ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡
Source:- Addis standard


















