ከ60 በላይ ወለሎች ይኖሩታል የተባለለትን ግዙፍ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ለመገንባት የተረከበው የመሬት ይዞታን የተነጠቀው አቢሲኒያ ባንክ፣ የተወሰደበት ዕርምጃ በልዩ ሁኔታ እንዲታይለት አቤቱታ ማቅረቡን ገለጸ፡፡
ባንኩ የዋና መሥሪያ ቤቱን ሕንፃ ለመግባት ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ ተረክቦት የነበረውን 9,700 ካሬ ሜትር የመሬት ይዞታ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነጥቆ ወደ መሬት ባንክ እንዲመለስ ካደረገ በኋላ፣ ለሌላ ልማት እንዲውል ማስተላለፉን ሰሞኑን በተካሄደው የባንኩ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተገልጿል።
ባንኩ የከተማ አስተዳደሩ የወሰደበት ዕርምጃ በልዩ ሁኔታ ታይቶ ይዞታው እንዲመለስለት ለተለያዩ የመንግሥት አካላት አቤቱታ አቅርቦ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን፣ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ መኮንን ማንያዘዋል ለጠቅላላ ጉባዔው አሳውቀዋል፡፡
በዚህ ቦታ ላይ ባንኩ የዋና መሥሪያ ቤቱን ሕንፃ ግንባታ ለማስጀመር የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶችን በማድረግና ግንባታውን እንዲያከናውን ከተመረጠው ቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ጋር የኮንትራት ስምምነት አድርጎ እንደነበርም ይታወሳል፡፡ በዚሁ ስምምነት መሠረት የቻይናው ኮንስትራክሽን ኩባንያ በተጠቀሰው ቦታ ላይ ግንባታውን ለመጀመር የሚያስችል የአፈር ማንሳትና የአፈር ደጋፊ (Sharing) ሥራዎች ጀምሮ እንደነበር አቶ መኮንን ማንያዘዋል ባቀረቡት ሪፖርት አስታውሰዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቢሲኒያ ባንክ ሕንፃ ለመገንባት ተረክቦት የነበረውን ቦታ ወደ መሬት ባንክ ካስገባ በኋላ በአሁኑ ወቅት ለታክሲ ተርሚናል አገልግሎት አውሎታል፡፡
አቢሲኒያ ባንክ በተነጠቀው በዚህ ይዞታ ላይ ለመገንባት አቅዶት የነበረው የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ 60 ወለሎች እንደሚኖሩትና ይህም የሕንፃውን ርዝማኔ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ቀዳሚ ያደርገዋል ተብሎ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ በርዝመቱ ተጠቃሽ የሆነው ሕንፃ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያስገነባው የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ሲሆን፣ ይህ ሕንፃ 209 ሜትር ርዝማኔ ያለው፣ አጠቃላይ 48 ወለሎቸ ያሉት ነው፡፡ አቢሲኒያ ባንክ ለመገንባት አቅዶ ያሠራው ባንክ ሕንፃ ግን 270 ሜትር ርዝማኔ ያለው ነበር፡፡
ምንጭ፡ ethiopianreporter


















