በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ያለውን መጠነ ሰፊ የኮሪደር ልማትና የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ማሻሻያ ተከትሎ፣ አባይ ሆምስ ሪል እስቴት (አባይ ቴክኖሎጂና ንግድ አ.ማ) ፕሮጀክቶቹን ከከተማዋ አዲስ ገጽታ ጋር በማስማማት በ2 ቢሊዮን ብር ወጪ የ”ኪንግስ ሬዚደንስ” አፓርትመንት ግንባታን በይፋ አስጀመረ።
ላለፉት 20 ዓመታት በአውቶሞቢል አስመጪነትና ገጣጣሚነት የቆየው ኩባንያው፣ ከሁለት ዓመት በፊት በቄራ (ፔፕሲ) አካባቢ ለመገንባት ያቀደው “ኪንግስ ሬዚደንስ” ፕሮጀክት በከተማዋ አዳዲስ የልማት ስራዎች ምክንያት ተቋርጦ የቆየ ቢሆንም፣ አሁን ላይ የዲዛይንና የይዘት ማሻሻያ በማድረግ ገዢዎች በተገኙበት የመሬት ቁፋሮ ስራውን ጀምሯል።
የፕሮጀክቶቹ ዝርዝር ሁኔታ፦
ኪንግስ ሬዚደንስ (Kings Residence)፦ በ668 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፍ፣ 22 ወለሎችና 80 የመኖሪያ አፓርትመንቶች ያሉት ሲሆን፣ 6 ወለሎችን ለፓርኪንግ የመደበና ለመጀመሪያ ጊዜ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች (EV) ቻርጅ ማድረጊያ ያካተተ ነው። ፕሮጀክቱ ለ200 ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል።
ዳውንታውን (Downtown)፦ በሜክሲኮ አካባቢ የሚገኝ 25 ወለሎች ያሉት የቅይጥ አገልግሎት (Mixed-use) ፕሮጀክት ሲሆን፣ 228 አፓርትመንቶችንና 220 ሱቆችን የያዘ ነው። ኩባንያው የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጠበት ሲሆን፣ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ክፍሎች በሽያጭ መተላለፋቸው ታውቋል።
የመተማመንና የዋጋ ግሽበት ችግሮችን ለመቅረፍ የተወሰዱ እርምጃዎች
የአባይ ሆምስ ሪል እስቴት አማካሪ አቶ ልኡል ደረጀ እንደገለጹት፣ በዘርፉ የሚታየውን የግንባታ ግብዓት የዋጋ ግሽበትና በቤት ገዢና አልሚ መካከል የሚፈጠርን አለመተማመን ለመቅረፍ ድርጅቱ የተለየ አሰራር ተከተሏል።
በዚሁ መሠረት፦
የዋጋ ግሽበትን መከላከል፦ ከመነሻው የዋጋ ግሽበቱን ታሳቢ ያደረገ ውል ማዘጋጀትና ደንበኞች ከዋጋ ጭማሪ ስጋት እንዲያመልጡ ከ10 በመቶ በላይ ቅድመ ክፍያ የመክፈል አማራጭ ማመቻቸት፣
ግልጽነትና መተማመን፦ ገዢዎች ግንባታው ከጅማሮው አንስቶ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በቦታው ተገኝተው ሂደቱን እንዲከታተሉ ማድረግ፣
ውል ማክበር፦ በተባለው የጊዜ ገደብ ውስጥ ቤት ባይረከቡ በአልሚው ላይ ቅጣት የሚያስጥል ውል መግባት የሚሉት ይገኙበታል።

















