አባይ ሆምስ የዳውንታውን ፕሮጀክቱን በሜክሲኮ አፍሪካ ህብረት አካባቢ በዛሬው እለት በይፋ አስጀምሯል።
ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በርካታ ተሽከርካሪዎችን በመገጣጠም፣ በመጠገን፣ በማስመጣት እና በመሸጥ የሚታወቀው አባይ የቴክኒክ እና ንግድ አ.ማ. ላለፉት ሁለት ዓመታት አባይ ሆምስ በሚል የንግድ ስያሜ ወደ ሪል እስቴት ልማት በመግባት ሜክሲኮ ጠማማ ፎቅ ፊት ለፊት በሚገኘው ይዞታው ላይ 3B+G+30 የሆነ እና በርካታ አገልግሎቶችን የያዘ ቅይጥ የንግድ እና የመኖሪያ ህንፃ ለመገንባት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱ በዛሬው እለት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተገልጿል።

የግንባታው ፕሮጀክት አጠቃላይ ተሰርቶ ሲያልቅ 576 አፓርትመንትና 700 የሚደርሱ የንግድ ሱቆችን የሚይዝ ሲሆን በአጠቃላይ 4.5 ቢሊየን ብር ወጪ ይፈጃል ተብሏል።
በ3 አመት ተኩል ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የታሰበው ይህ ዳውን ታውን ፕሮጀክት በካሬ ከ81,000 ብር ጀምሮ የአፓርትመንት ቤቶችን በመሸጥ ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል።
150 የሚደርሱ ቋሚ ሰራተኞች ያሉት ሲሆን ይህ ዳውን ታውን ፕሮጀክት ከ500 በላይ ለሆኑ ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራል።
በመግለጫው እንደተገለጸው በሪል እስቴት ዘርፉ ላይ የወጡ አዳዲስ የመንግስት ፖሊሲዎች በፕሮጀክቱ አጀማመር ላይ ትልቅ ተግዳሮት ፈጥረው እንደነበር ተገልጿል።
ምንጭ: ጌጡ ተመስገን


















