‹ጎዶ ሪል እስቴት› በሚል ስያሜ መርካቶ አካባቢ እንደሚገነባ የተነገረለት ይህ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘመናዊ የተባሉ ቴክኖሎጂዎችን ያካተተ እንደሆነ የድርጀቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ደረጄ ማሙዬ ገልጸዋል፡፡
በአፍሪካ ሆልዲንግ ግሩፕ ስር የሚተዳደረው የመኖሪያ መንደሩ ዘመናዊ አሠራርን የተላበሰ፤ የብረት ፍጆታን መቀነስ የሚያስችሉ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የሚጠቀም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሚቀጥሉት 5 ዓመታት 500 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት መታቀዱን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፤ መንግሥት 30 በመቶ በሚሆነው ሥራና ሀብት ላይ እንደሚሳተፍ አስታውቀዋል፡፡
የሪል እስቴት ግንባታው ከአፍሪካ ትልቁ የገበያ ማዕከል በሆነው መርካቶ አካባቢ መገንባቱም ለየት እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡
26 ሊፍቶች፣ ከ2 ሚሊዮን ሊትር በላይ ውኃ ማጠራቀሚያ፣ የሄሊኮፕተር ማረፊያ፣ የሕክምና አምቡላንስ አገልግሎት እንዲሁም የአደጋ ጊዜ መጠበቂያ እና የሕፃናት መጫወቻ ስፍራዎችን አጠቃሎ የሚይዝ ይሆናል ተብሏል።
አፍሪካ ሆልዲንግ ግሩፕ ‹ጎዶ ሪል እስቴትን› በ27 ቢሊዮን ብር ወጪ በመገንባት የቤት ፍላጎትን ከማቃለል በተጨማሪ፤ በተለያዩ ማኅበራዊ ኃላፊነቶች ላይ እንደሚሳተፍ የድርጀቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ደረጄ ማሙዬ ገልጸዋል፡፡
ምንጭ: መናኸሪያ ሬዲዮ


















