ኦቪድ ሪል እስቴት ለገቢዎች ሚኒስቴርና ለጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች ከ5ሺህ በላይ የመኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት በዛሬው ዕለት ከተቋማቱ አመራሮች ጋር ተፈራርሟል።
የኦቪድ ሆልዲንግ መስራተችና ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ ታደሰ ኦቪድ ሪል እስቴትን በመወከል የመግባቢያ ስምምነቱን ከገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ እና ከጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቀበታ ጋር የተፈራረሙ ሲሆን፣ ስምምነቱ የተቋማቱ ሰራተኞች ከኦቪድ ገላን ጉራ ከተማ ፕሮጀክት ተደራሽነት ያላቸውና ምቹ የመኖሪያ ቤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በተለያዩ አማራጮች ለመግዛት እንዲችሉ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው ተብሏል።
በኦቪድ ገላን ጉራ ከተማ ፕሮጀክት የሽያጭ ማዕከል በተካሄደው የፊርማ ስነስርአት ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኦቪድ ሆልዲንግ መስራተችና ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ ታደሰ፤ የሁለቱም ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች በኦቪድን በመምረጣቸውና እምነት በመጣላቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ስምምነቱ ኦቪድ ሪል ደረጃቸውን የጠበቁ የመኖሪያ ቤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የመንግስት ሰራተኞችን ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይና በአቅርቦት ሰንሰለቱ ውስጥ የሚገኙት ሁሉም የኦቪድ እህት ኩባንያዎች ለተፈጻሚነቱ እጅ ለእጅ ተያይዘው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።
ኦቪድ ሪል እስቴት የተቋማቱን ሰራተኞች ምርጫ፣ አቅምና ፍላጎት ባማከለ መልኩ ቤቶቹን በተገቢው የጥራት ደረጃና በፍጥነት ገንብቶ እንደሚያስረክብም ቃል ገብተዋል።
የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ በበኩላቸው የመኖሪያ ቤቶች አቅርቦት በመንግስት ጥረት ብቻ ሊሟላ የማይችል ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው፣ ኦቪድ ሪል እስቴት በመንግስትና የግሉ ዘርፍ ሞዳሊቲ እያከናወናቸው የሚገኙ የቤት ልማት ስራዎችና አጠቃላይ የልማት እንቅስቃሴዎች በዚህ ረገድ በአብነት የሚጠቀሱና የሚበረታቱ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ስምምነቱ የተቋማቱ ሰራተኞች ገንዘባቸውን በመቆጠብ እንደየ አቅምና ፍላጎታቸው በተመጣጣኝ ዋጋ የቤት ባለቤት የሚሆኑበትን ዕድል የሚፈጥር ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ይህም ስራቸውን ተረጋግተው በሙሉ ትኩረት ለማከናወን ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል።
የተቋማቱ ሰራተኞች ይህንን ታላቅ ዕድል በአግባቡ እንዲጠቀሙና ገንዘባቸውን ከወዲሁ በመቆጠብ በቀጣይ በሚወጣው አሰራር መሰረት ክፍያቸውን በመፈጸም የቤት ባለቤት እንዲሆኑ የአደራ መልዕክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን፤ ኦቪድ ሪል እስቴት ቤቶቹን በተገቢው የጥራት ደረጃ በወቅቱ አጠናቅቆ እንደሚያስረክብ ያላቸውን ተስፋም ገልጸዋል።
የፊርማ ስነ-ስርአቱን ተከትሎ የኦቪድ አመራሮች በኦቪድ ገላን ጉራ ከተማ ፕሮጀክት የሽያጭ ማዕከል የሚገኙትን ሞዴል መኖሪያ ቤቶች በስነ-ስርአቱ ላይ ለተገኙት የሁለቱም ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች አስጎብኝተዋል።
ምንጭ፡ ኦቪድ ሆልዲንግ


















