ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተባበሩት መንግሥታት የሰው ሰፈራ ፕሮግራም (UN-Habitat) ጋር በመሆን የአዲስ አበባን ዘላቂ ልማት በጋራ ለማጠናከር የሚያስችል የትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል።
ይህ ስምምነት የከተማዋን አስተዳደር አሰራር በማሻሻል ለነዋሪዎች የተሻለ የኑሮ ሁኔታን ለመፍጠር ትልቅ እገዛ የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል።
ሁለቱ አካላት የተፈራረሙት ስምምነት በበርካታ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ በከተማ መረጃ አሰባሰብና ትንተና፣ በልማት ውጤቶች ክትትል እና የ11ኛው የመዋቅራዊ ፕላን ዝግጅት ላይ በጋራ ለመስራት ያስችላል።
ከዚህ በተጨማሪም በተመጣጣኝ ዋጋ የቤት አቅርቦትን ማሻሻል እና ከCOP32 ጋር የተያያዙ የከተማ ዝግጅቶችን ማቀናጀት በስምምነቱ ዋና ዋና ትኩረት የተሰጣቸው አጀንዳዎች ናቸው።
ይህ አጠቃላይ ትብብር የከተማ አስተዳደር አቅምን ከፍ በማድረግ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለማስፋትና እና የነዋሪዎችን የኑሮ ሁኔታ በዘላቂነት ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተገልጿል።
ምንጭ:- የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ


















