የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት የቦሌ ሹቡ ኤጀርሳ የተቀናጀ ነዋሪዎች መንደር ለአካባቢው የልማት ተነሺዎች ማስረከባቸውን አስታውቀዋል።
ከንቲባዋ የከተማ ልማት ዋነኛ ዓላማ መሠረተ ልማትን መገንባት ብቻ ሳይሆን የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል፣ መብትና ጥቅም ማስጠበቅ እንዲሁም የተሻለ የኑሮ ዕድል መፍጠር እንደሆነ ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ እየተገነባ የሚገኘው የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ዩኒቨርሲቲ የሀገራችንን የቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ እድገት የሚያፋጥን ትልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ ቀደም ሲል መሬቱን ለእርሻ፣ ለግጦሽና ለመኖሪያነት ሲጠቀሙ የነበሩ አርሶ አደሮችን ሕይወት የሚነካ በመሆኑ የልማቱ ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ እንዳይሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል።
በዚሁ መሠረት ለሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ልማት ከእርሻና መኖሪያ ቦታቸው ተነሺ ለሆኑ የቦሌ ሹቡ ኤጀርሳ አርሶ አደሮች የተቀናጀ መኖሪያ መንደር ተገንብቶ የኑሮና የገቢ ምንጮቻቸውን የሚያሳድጉ አቅርቦቶች ተካተዋል።

ይህ አሠራር የነዋሪዎቹን ማኅበራዊ ትስስር ጠብቆ ወደ ተሻለ የአኗኗር ሁኔታ የሚያሸጋግር ሰው ተኮር የልማት አሠራር መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አብራርተዋል።
ከመኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ መንደሩ የወተት ላሞችን የሚይዙ የከብት ሼዶችና የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ፣ የንግድ ሱቆች፣ የምርት ማከፋፈያና መሸጫ መጋዘን እንዲሁም ወፍጮዎችን አሟልቷል።
በተጨማሪም የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የሕፃናት መጫወቻና ማቆያ ማዕከል እና የስብሰባ አዳራሽ የተካተቱ ሲሆን፣ እነዚህ አቅርቦቶች ነዋሪዎቹ የተሻለ መኖሪያ እንዲኖራቸው፣ የወተት ልማትና ሌሎች የገቢ ምንጮቻቸውን እንዲያሳድጉ፣ ማኅበራዊ ትስስራቸውን እንዲጠብቁ እና ልጆቻቸው ምቹ አካባቢ እንዲያገኙ ታስበው የተዘጋጁ ናቸው።

ልማት ማለት ሰውን ከነበረበት ቦታ ማንሳት ብቻ ሳይሆን የኑሮ ደረጃውን ማሻሻል፣ የኢኮኖሚ አቅሙን ማጠናከርና የነገ ተስፋውን ማለምለም ጭምር እንደሆነ የገለጹት ከንቲባዋ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ቦታው ለታላቅ ሀገራዊ ፋይዳ እንደሚውል ሲያስረዷቸው ዩኒቨርሲቲው ለልጆቻቸው የመማር ዕድልና ሀገርን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የመሆን አቅም እንደሚፈጥር በመገንዘብ በፈቃደኝነት ትብብር ማድረጋቸውን ጠቅሰው ከልብ አመስግነዋል።
ይህ ተግባር በመደመርና በትብብር ሲሠራ ሁሉንም ወገኖች ተጠቃሚ ማድረግና ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ እንደሚቻል ማሳያ እንደሆነና የቦሌ ሹቡ ኤጀርሳ ነዋሪዎች መንደርም ይህንኑ ሰው ተኮር የልማት አቅጣጫ በተግባር የሚያሳይ ምሳሌ መሆኑ ተጠቅሷል።
የምንገነባት አዲስ አበባ የሁሉም ነዋሪዎቿን ክብር፣ መብትና ጥቅም የምታስጠብቅና ሁሉንም በእኩል የልማት ተጠቃሚ የምታደርግ ከተማ እንድትሆን አስተዳደሩ ቁርጠኛ መሆኑን በማረጋገጥ፣ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለቦሌ ክፍለ ከተማ አመራሮችና በሥራው ሂደት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።


















