ለሀገራችን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ እድገት ከፍተኛ ሚና የሚጫወት አዲስ የፕሮጀክት ፊዚካል አፈጻጸም መለኪያ ስታንዳርድ ነሐሴ 26/2018 ይፋ ተደርጓል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማና መሠረተ-ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም የዘርፉ ተዋናዮችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት አዲስ የተዘጋጀው የስታንዳርድ ማዕቀፍ አዲስ አበባ በሚገኘው ሀርመኒ ሆቴል ላይ በተዘጋጀ መድረክ ይፋ ተደርጓል።
በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መስፍን ነገዎ (ዶ/ር) እንደገለጹት ስታንዳርዱ የአንድ ፕሮጀክት አፈጻጸምን ብቻ ለመለካት ሳይሆን፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ብቃት፣ ምርታማነት፣ ጥራትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ወሳኝ ሚና አለው።
በዋናነትም ሀገራዊ የኮንስትራክሽን የኢንዱስትሪውን ብቃት በማሳደግ፣ ምርታማነትንና የፕሮጀክት ጥራትን በማሻሻል፣ መዘግየትን በመቀስ እና ተጠያቂነትን በማስፈን ረገድ የላቀ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
አያይዘውም የኢንዱስትሪን መረጃ አስተማማኝ በማድረግ ፣ የኢንቨስትመንት እምነትን በማሳደግ እና የኮንትራክተሮችን ተወዳዳሪነት በማሳደግ ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ብለዋል ዶ/ር መስፍን ነገዎ።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን የተሰጠውን ተልዕኮና ኃላፊነት በብቃት ለመፈጸም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመደመር መርህ በጋራ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አውስተው በአገር አቀፍ የዘርፉ ደረጃ አዲስ የሆነው የግንባታ ፕሮጀክቶች ፊዚካል አፈጻጸም መለኪያ ስታንዳርድ ማዕቀፍ እውን እንዲሆን ተቋሙ የአጋርነት ሚና መጫወቱን ገልጸዋል።
በቀጣይም የስታንዳርድ ማዕቀፉ ወደ ተግባር እንዲሸጋገር ለማድረግ ባለስልጣን ተቋሙ አጋርነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና የዘርፉ ተዋናዮችና ባለድርሻ አካላትም ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ዶ/ር መስፍን ነገዎ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ምንጭ:- የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን
















