ጀንቦሮ ሪል እስቴት በአምስት አመት ውስጥ አራተኛውን ፕሮጀክቱ የሆነውን ቡልቡላ ኘሮጀክት የሚገኘውን አፓርትመንት አስመረቀ። የኩባንያው የሽያጭ እና ግብይት ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዘላለም ምህረቱ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት ከሆነ ኩባንያው ለ120 ደንበኞች በድምሩ 80 አፓርትመንቶች እና 40 ሱቆች አስረክቧል።
አቶ ዘላለም ፕሮጀክቱ በሁለት አመት ከስድስት ወር ጊዜ ውስጥ መጠናቀቁን ገልፀው፣ ይህ በሰዓቱ የማስረከብ ስራ የጀንቦሮ ሪል እስቴት “በጊዜ ግቡ” የሚለውን መርህ የሚያሳይ ነው ብለዋል። ይህ በአጭር ጊዜ ውስጥ አራት ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ የኩባንያው ትልቅ ስኬት እንደሆነም አክለዋል።
የጀንቦሮ ሪል እስቴት በቀጣይነት ለመስራት ያቀዳቸውን ፕሮጀክቶችም አስመልክተው አቶ ዘላለም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

- ቡልቡላ ፕሮጀክት: በቡልቡላ የሚገኘው የድርጅቱ አምስተኛ የአፓርትመንት ፕሮጀክት ከስምንት ወራት በኋላ ለአገልግሎት የሚበቃ ሲሆን፣ አሁን ላይ ግንባታው የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።
- ሳር ቤት ኪሩ ፕሮጀክት: ቫቲካን ኢምባሲ አጠገብ የሚገኘው ይህ ፕሮጀክት በጣም ትልቅ በሆነ ኢንቨስትመንት ግንባታው እና ሽያጩ በፍጥነት እየተከናወነ ሲሆን፣ ባለ 30 ፎቆችን እና ለኑሮ የሚያስፈልጉ እንደ የልጆች መጫወቻ ስፍራ፣ ጂም፣ ስፓ የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ያካተተ ነው።
- ተጨማሪ የሳር ቤት ፕሮጀክት: ኩባንያው በዚሁ በሳር ቤት አካባቢ ሌላ ሁለተኛ ፕሮጀክትም እየገነባ ሲሆን፣ ሽያጩ ባይጀመርም ግንባታው 30 በመቶ ደርሷል።
በመጪው አመት የጀንቦሮ ሪል እስቴት በአመት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ አፓርትመንቶችን ለመገንባት የሚያስችሉ አዳዲስ የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂዎችን ለመግዛት እቅድ እንዳለውም አቶ ዘላለም ተናግረዋል።
የጀንቦሮ ሪል እስቴት ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ዮናስ ብርሀኔ ፤ ፕሮጀክቱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ 2 አመት ከ 6 ወራት ጊዜ ብቻ እንደወሰደ ገልጸው ድርጅቱ ለኮንስትራክሽን ስራው ግብዓት የሚያቀርቡ የኮንክሪት ሚክስ፣ የአሸዋ እና ጠጠር አምራች እህት ኩባንያዎችን አቋቁሞ የሪል እስቴት ስራውን እንዲደግፉ ማድረጉ በ 5 አመታት ውስጥ 4 የአፓርትመንት ፕሮጀክቶችን ከተዋዋለበት ጊዜው አስቀድሞ ገንብቶ ለደምበኞቹ በፍጥነት ለማስረከብ እንዳስቻለው ገልጸዋል፡፡


















