ዝቋላ ሪል እስቴት (Ziquala Real Estate) በሲኤምሲ አካባቢ በስኬት ያስገነባውን “ሂል ሳይድ አፓርትመንት” የተሰኘ ዘመናዊ የመኖሪያ አፓርትመንት ፕሮጀክት ባሳለፈው ቅዳሜ ለቤት ባለቤቶች ሙሉ ለሙሉ በማስረከብ የርክክብ መርሐ ግብር አካሂዷል።
ይህ ታላቅ የምረቃና የርክክብ መርሐ ግብር የኩባንያውን ከፍተኛ ቁርጠኝነት፣ የሥራ ጥራትና የኃላፊነት ስሜት የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ ለቤት ገዢዎች የገባውን ቃል በተግባር ማረጋገጡን ያሳየ ትልቅ ምዕራፍ ሆኖ ተመዝግቧል።
የኩባንያው ባለቤት እና ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አብርሃም ደምሴ እንደገለጹት፣ ህንፃው በ1,400 ስኩየር ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን የአጠቃላይ ቦታው ስፋት ደግሞ ወደ 2,800 ካሬ ሜትር አካባቢ ይደርሳል።
በውስጡ 63 አፓርትመንቶችን የያዘው ይህ ፕሮጀክት በሦስት የተለያዩ የቤት ዓይነቶች የተዋቀረ ሲሆን፣ እነሱም 271 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው 27 ቤቶች፣ 150 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው 18 ቤቶች እንዲሁም 125 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው 18 ቤቶች ናቸው።
የግንባታ ሂደቱን በተመለከተ ኢንጂነር አብርሃም አክለው እንደገለጹት፣ የዚህ ዘመናዊ ህንፃ ግንባታ ሥራ ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል ሲከናወን ቆይቷል።
ዝቋላ ኮንስትራክሽን በግንባታው ዘርፍ በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ስምና ጠንካራ መሠረት የገነባ ተቋም ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ያንን ታላቅ የሥራ ልምድና አስተማማኝነት በሪል እስቴት ዘርፍ ውስጥ በድምቀት እያሳየ ይገኛል።
ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ቤት ገዢዎች ቀደም ሲል ወደ ቤቶቻቸው ገብተው ሕይወታቸውን መጀመራቸው ሲሆን፣ ይህም የፕሮጀክቱን ስኬትና ተግባራዊነት ይበልጥ ጎልቶ እንዲታይ አድርጎታል።
ኩባንያው የመጀመሪያውን የሪል እስቴት ፕሮጀክት በአያት አካባቢ ገንብቶ ከዚህ ቀደም ያስረከበ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ አዳዲስ ፕሮጀችቶችን በቦሌ አትላስ ወንዝ ዳርቻ (Atlas River Side)፣ 22 ከአዲስ ሕይወት ሆስፒታል ፊት ለፊት እንዲሁም ከግሪክ ትምህርት ቤት ተቃራኒ እየገነባ ይገኛል።

















