የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ በምደባና በጨረታ መሬት ወስደው ለረጅም ጊዜ ያለ አገልግሎት መሬት አጥሮ የያዙ የ50 አልሚዎችን ውል ማቋረጡን የመሬት ዝግጅትና ማስተላለፍ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ፌኑስ ገላና ተናግረዋል።
ኃላፊው ይህን የተናገሩት በተለያየ አግባብ መሬት ወስደው ያለ ልማት ለረጅም ጊዜ አጥሮ የያዙ አልሚዎች ወደ ልማት ያልገቡበትን ምክንያት የጋራ ለማድረግ በተደረገ ውይይት ላይ ነው።
መንግሥት ላለፉት ዓመታት የከተማውን ኢኮሮሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎት ለማቀላጠፍ በዝቅተኛ የሊዝ ክፍያ መሬት በምደባ ማስተላለፉን የገለፁት ምክትል ቢሮው ኃላፊው ፤ ሆኖም በርካታ አልሚዎች በገቡት የሊዝ ውል መሰረት ግንባታ ለመጀመር እና ለማጠናቀቅ ፈቃደኛ አልበሩም ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ መሬት በምደባ እንዲያገኙ ከተላለፉ የካብኔ ውሳኔዎች በተደጋጋሚ ጥሪ ቢቀርብም 100 አልሚዎች የሚጠበቅባቸውን የሊዝ ቅድመ ክፍያ ከፍለው ወደ ስራ ለመግባት ዝግጁ እንዳልሆኑ ለማሳያነት የጠቆሙት ኃላፊው አልሚዎች እርምጃ ከመወሰዱ በፊት መንግሥት ያመቻቸውን ተጨማሪ እድል በመጠቀም ወደ ልማት እንደሚገቡ አሳስበዋል።
ምንጭ፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ

















