ሜሪት ፕሮፐርቲስ ከዲቦራ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ከአእምሮ እድገት ውስንነት ጋር ለተወለዱ ህጻናት የሙያ ክህሎት ስልጠና የሚሰጥ አዲስ ወርክሾፕ ግንባታ ጀመረ።
ዲቦራ ፋውንዴሽን ከአእምሮ እድገት ውስንነት ጋር ለተወለዱ ህጻናት ድጋፍና እንክብካቤ የሚሰጥ ተቋም ሲሆን፣ አዲሱ የሙያ ስልጠና ማዕከል ህጻናቱ አቅማቸውን እንዲያዳብሩ፣ ተሰጥኦዎቻቸውን እንዲያበለጽጉና የሙያ ክህሎት እንዲያገኙ ዕድል ይፈጥራል።
በ344 ካሬ ሜትር ስፋት ላይ የሚገነባው ማዕከሉ በአንድ ወር ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱ ተገልጿል። በማዕከሉም በጥናት የተመረጡ 11 የሙያ ዘርፎች ላይ ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን፣ ልብስ ስፌት፣ ጌጣጌጥ፣ ዳንቴልና ኤፖክሲ ሥራዎች ከሚሰጡት ስልጠናዎች መካከል ይገኛሉ።
የስልጠና ዘርፎቹ የህጻናቱን አቅምና ደህንነት በጥናት ያገናዘቡ መሆናቸውን የገለጸው ሜሪት ፕሮፐርቲስ፣ ፕሮጀክቱ ህንፃ ከመገንባት ባለፈ ክህሎትን ለመገንባት፣ አቅምን ለማጎልበትና ለህጻናቱ የተሻለ የወደፊት ዕድል ለመፍጠር ያለመ መሆኑን አስታውቋል።
ይህ ትብብር የሚመጣው ሜሪት ፕሮፐርቲስ “አንድ ዓመት፣ አንድ ራዕይ – ቀጣዩ ምዕራፍ” በሚል መሪ ቃል የአንድ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን ባቀረበበት ወቅት ሲሆን፣ ኩባንያው ባሳለፈው ዓመት ከ24 በላይ ቤቶችን ለአቅመ ደካሞች ሙሉ ወጪውን በመሸፈን እንዳስገነባ ተገልጿል።
የዲቦራ ፋውንዴሽን ጋር የተጀመረው ይህ የሙያ ማሰልጠኛ ማዕከል በቀጣይ በህጻናቱ ክህሎት እድገትና ተሳትፎ ላይ ተጨባጭ ሚና እንዲኖረው የታቀደ ሲሆን፣ ሜሪት ፕሮፐርቲስም በቀጣይ የማህበራዊ ኃላፊነት ተግባራቱን እንደሚያጠናክር አስታውቋል።
ምንጭ፦ Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)


















