አፍታ ሜይራ ሪል እስቴት እያስገነባቸው በሚገኙ ዘመናዊ ቤቶች ላይ 25/75 የብድር አቅርቦት ማዘጋጀቱን ዛሬ ነሐሴ 1 2016 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አሳውቋል።
በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተገለጸው ስምምነቱ በዋናነት በተለይ ለሀገራችን የቤት ፈላጊዎች እና የፋይናንስ ፍላጎትን ለመፍታት ታሳቢ ያደረገ ስምምነት ነው ተብሏል።
ለዚህም ስራ መቀላጠፍ ከብራይት ገንዘብ ቁጠባና ብድር ተቋም ለቤት ፈላጊዎች ከብድር ጋር በተያያዘ የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ በቀጣይም አብረው የሚሰሩባቸውን ዝርዝር ጉዳዮች ላይ የጋራ ውል ከሰሞኑ መፈፀማቸው ይታወሳል።
በአፍታ ሜይራ ግሩፕ ስር የሚገኘው አፍታ ሜይራ ሪል እስቴት በቦሌ ቡልቡላ እና ጎፋ መብራት ሀይል ሳይት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማስገንባት ላይ የሚገኘውን ዘመናዊ ቤቶችን ለቤት ፈላጊው እጅግ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ እያቀረበ እንደሚገኝ አስታወቋል። አፍታ ሜይራ ሪል እስቴት የቤት ችግርን ዘመኑን በሚመጥን ተፈጥሯዊ ውበት የተላበሱ ቤቶችን በዓለማቀፉ SAGA እና FOG የዲዛይን ንድፍ ሐሳብ በመገንባት እና በመሸጥም ላይ ይገኛል።
ከቴክኖሎጂ ጋር የተዋሃደ ፣ከተፈጥሮ ጋር የታረቀ ፣እውነተኛ ቅናሽ የተደረገባቸው ፣ለዓለምም ጭምር አዲስ በሆነው በFOG/Futuristic Organic Green ንድፈ ሐሳብ የሚገነቡ ቤቶችን በቅናሽ አቅርበናል ብለዋል።

በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ቆጥበው አልያም አስቀድመው 25 በመቶ መክፈል የሚችሉ ደንበኞችን የቤት ባለቤት አደርጋለሁ ብሏል። 15 ፕሮጀክቶችን ይዘው መምጣታቸውን እና አሁን ላይ ሁለቱ ፕሮጀክቶች ወደ ስራ መግባታቸውን የገለፁት የአፍታ ሜይራ ግሩፕ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አሚር አብዱልዋሀብ ናቸው። ደንበኞች ለቤት ሲመዘገቡ ገንዘቡን ለአፍታ ሜይራ ግሩፕ የሚከፍሉት ሳይሆን በብራይት ብድርና ቁጠባ በከፈቱት የግል አካውንታቸው የሚያስቀምጡት መሆኑንም ተናግረዋል።
ግፋ ቢል እስከ 1 ዓመት ከ6 ወር ድረስ ቤቱን እንደሚያስረክብ የገለፁት አቶ አሚር፤ በመጀመሪያው አንድ አመት ጊዜ ውስጥ ግን የቤት ባለቤት መሆን እንደማይቻል ነው ያነሱት። ቀሪውን ክፍያ ደግሞ እስከ 10 ዓመት ባለው ጊዜ ቤቱን እየኖሩበት የሚከፍሉት ነው ብለዋል።
25 በመቶ ክፍያው እንደየቤቱ መጠን የተለያየ መሆኑም የተነሳ ሲሆን ፤ ቅድሚያ የሚከፍሉ በቅድሚያ ቤታቸውን የሚያገኙ መሆኑን ነው አቶ አሚር የተናገሩት። 75 በመቶ የሚሆነው የብድር መጠን እስከ 10 ዓመት ጊዜ ተከፍሎ የሚያልቅ መሆኑም ተነስቷል። የወለድ ምጣኔው ለሴቶች እና ለወንዶች የተለያየ ሲሆን፤ ከ14.5 በመቶ እስከ 15.5 በመቶ ድረስ የሚታሰብ ነው። እነዚህ ፕሮጀክቶች በቦሌ ቡልቡላ፣ ለቡ መብራት፣ ጎፋ መብራት እና መገናኛ አከባቢ የሚሰሩ ናቸው።
አፍታ ሜይራ ግሩፕ ኃ/የተ/የግ/ማ ላለፋት በርካታ አመታት በኢንፓርት ኤክስፖርት ፣በኮንስትራክሽን፣ በሪል እስቴት፣ እና በቴክኖሎጂ ላይ የተሰማራ ድርጅት ነው።
ምንጭ፡ ድሬ ትዩብ ሪፖርተር እና ethioexplorer


















