በዘንድሮው ዓመት 2018 በአዲስ አበባ ከተማ” የኮሪደር ስራ” ተብሎ እንደ አዲስ የሚጀመር ስራ እንደማይኖር ፤ የዘንድሮ ትኩረት ቤቶችን መገንባት እና የውሃ አቅርቦትን ማሻሻል እንደሆነ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይህን ያሉት ለአዲስ አበባ ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ነው።
በማብራሪያቸው እስካሁን በኮሪደር ስራ የተገኙ ውጤቶች ከከተማው ስፋት አንጻር ገና እንደሆነ ገልጸዋል።
ስራዎቹ የተሰሩት ታቅዶባቸው፣ የበጀት ዝግጅት ተደርጎ፣ ቤቶች ተዘጋጅተው ፣ የበጀት ቅደም ተከተል ተስተካክሎ መሆኑን አንስተዋል ፤ ስራው ሰፊ ዝግጅት የሚፈልግ እንደሆነም አመልክተዋል።
በዚህም በዘንድሮ ዓመት 2018 በከተማው ‘ የኮሪደር ስራ ‘ ተብሎ እንደ አዲስ የሚጀመር ነገር እንደማይኖር አሳውቀዋል።
“የ2018 ትልቁ ትኩረት የቤት ግንባታና የውሃ አቅርቦት ነው ብለን አፀድቀናል ምክር ቤቱን” ያሉት ከንቲባ አዳነች” ዘንድሮ ዋናውና ትልቁ ትኩረታችን የመኖሪ ቤት ግንባታ ይሆናል ብለዋል።
ይህም ቢሆን ግን ስታንዳርዳቸውን መጠበቅ ያለባቸው የከተማው መንገዶች እንደሚሰሩ ፣ እንደሚታደሱ አመልክተዋል።
እነዚህ መንገዶች የትራፊክ ፍሰቱን የሚያስተካክሉ፣ ቅድሚያ የሚሰጣቸው፣ ህዝብ የጠየቃቸው መንገዶች እንደሆኑ ተናግረዋል።
የመንገዶቹ ስራ ሲሰራም የኮሪደር ልማት ስታንዳርድን እንደሚከተሉ ገልጸዋል።
- የተሽከርካሪ መንገዶች ስራና እድሳት
- የተሽከርካሪ መንገዶች ማስፋት ስራ
- የእግረኛ መንገዶች ስራ
- የሳይክል መንገዶች ስራ እንደሚኖር ጠቁመዋል።
“ሁሉንም በአንዴ መጀመር አንችልም። አሁን ላይ አጥንተን የጨረስነው ከዑራኤል – ቦሌ ብራስ VIP የሚገናኘው ነው እሱ እየተሰራ ነው። በፍጥነት ካልሰራነው ቢዝነስ ላይ ተፅእኖ ያሳድራል ፣ በአካባቢው ላይ የትራፊክ ፍሰቱ ላይ ጫና ያሳድራል ለዛም የጀመርነውን በፍጥነት እየጨረስን ነው ሌላ የምንጀምረው” ብለዋል።
“በዚህ አመት ኮሪደር ብለን እንደ አዲስ የምንጀምረው አይኖርም፤ ጥናት እናደርጋለን ቤቶችን እንገነባለን፣ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል በተባሉት ላይ ከህዝብ ጋር ውይይት እናደርጋለን ፣ ተግባቦት እንፈጥራለን” ሲሉ አስረድተዋል።
የመንገድ ግንባታዎች ግን ፦
- ቀድሞ የተጠየቁ፣
- የተጀመሩ ፣
- ከልማት ተነሺዎች ጋር ችግሮች ገጥመዋቸው የነበሩ በራስ ኃይል መሰራታቸውን እንደሚቀጥሉ አሳውቀዋል።
ምንጭ፡ ቲክቫህ ኢትዮጵያ


















