የኢትዮጵያን የመስታወት ፍላጎት 90 በመቶ ማሟላት የሚችልና በቀን ከ600 ቶን በላይ ማምረት የሚያስችል ፋብሪካ፣ በወቅቱ ምንዛሪ ከ14.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወይም ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ሊገነባ መሆኑን፣ ኤኤምጂ ሆልዲንግ ኢንዱስትሪ አስታወቀ፡፡
ፋብሪካው በዋናነት ሁለት ዓይነት የመስታወት ምርቶችን እንደሚያመርት ለሪፖርተር የተናገሩት የኤኤምጂ ሆልዲንግ ኢንዱስትሪ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ጌጡ፣ የመጀመሪያው “ፍሎት ግላስ” የሚባል ሕንፃዎች ላይ የሚገጠምና ለሌሎች መሰል አገልግሎት የሚውልና በቀን እስከ 600 ቶን የሚመረት ነው፡፡
ሁለተኛው ፋብሪካ “ኮንቴይነር ግላስ” የተባለና ለምግብ፣ ለመጠጥ፣ ለመድኃኒትና ለመዋቢያነት የሚያገለግሉ ጠርሙሶች የሚያመርት መሆኑን፣ በቀን ከ60 ቶን በላይ ጠርሙሶችን እንደሚያመርት አቶ ሰለሞን አክለዋል፡፡
ሁለቱን የማምረቻ ፋብሪካዎች ለማቋቋም ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚፈጅ ያስረዱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ለ2,500 ሠራተኞች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡
ኤምኦዩ የተባለ የቻይና ኩባንያ የፋብሪካ ማሽኖችን እንዲያቀርብ ከስምምነት መድረሱን የተናገሩት አቶ ሰለሞን፣ ግንባታው ሲጠናቀቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማሽኖችን በማስገባት በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምር ገልጸዋል፡፡
የአገር ውስጥ ግብይቶችን በዋናነት ይጠቀማል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ 70 በመቶ የሚሆነውን ግብዓት ልዩ ከሆነ አሸዋና ሌሎች ግብዓቶችን ጨምሮ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ጥሬ ዕቃዎች አገር ውስጥ የሚገኙ ናቸው ብለዋል፡፡
መስታወት በአብዛኛው ከውጭ የሚገባ መሆኑን የገለጹት አቶ ሰለሞን፣ በበቂ ሁኔታ ለማምረት መዘጋጀታቸውንና ሁሉንም ዓይነት መስታወቶች አምርቶ ለማቅረብ መታሰቡን ተናግረዋል፡፡
በሰኔ 2017 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባውን ሲያደርግ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በዓመት 600 ሺሕ ቶን የማምረት አቅም ያለው የመስታወት ፋብሪካ አቃቂ አካባቢ እየተገነባ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች በመሆኑ በዘርፉ ዕድገት እየተመዘገበ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ፋብሪካው ዘመናዊ የኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚፈልገውን የመስታወት ምርት በጥራት ለማቅረብ የሚችል መሆኑን ተናግረው ነበር።
ኢትዮጵያ በቂ የመስታወት ፋብሪካ እንዳልነበራት ገልጸው፣ አሁን የአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃ ሙሉ ለሙሉ የሚጠቀም ፋብሪካ መገንባት መጀመሯን መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
አዳዲስና ነባር የለስላሳ መጠጦች፣ ጠርሙሶችና ሌሎች መስታወቶች የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ሲኖሩ፣ አዲስ አበባ ጠርሙስና ብርጭቆ አክሲዮን ማኅበር፣ በቅርቡ በደብረ ብርሃን ከተማ ሥራ የጀመረውና በዓመት እስከ 200 ሚሊዮን የመስታወት ጠርሙሶችን የማምረት አቅም ያለው ጁኒፐር ፋብሪካና ሊሎችም መሰል ፋብሪካዎች ይገኛሉ።
በአገር ውስጥ የጠርሙስና የመስታውት ምርቶች ፍላጎት ከፍተኛ ሲሆን፣ ይህንን ፍላጎት ለማሟላት የአገር ውስጥ አምራቾች በቂ ባለመሆናቸው አሁንም በርካታ የጠርሙስ ምርቶች ከውጭ እንደሚገቡ መረጃዎች ያሳያሉ።
ኤ.ኤም.ጂ ሆልዲንግ እ.ኤ.አ በ2010 የተመሠረተ አገር በቀል ኢንዱስትሪ ሲሆን፣ በብረታ ብረት ኢንዱስትሪና ተዛማች መስኮች እንዲሁም በዘይትና በቅባት እህሎች ምርት አቅርቦት፣ በሪልስቴት ዘርፍና የቡና ምርትን ወደ ተለያዩ አገሮች በመላክ የሚታወቅ ሲሆን፣ ቆርቆሮዎችን ጨምሮ ሌሎች የግንባታ ዕቃዎችን በማምረት ላይ የሚገኝ ነው፡፡
ድርጅቱ እ.ኤ.አ በ2030 በምሥራቅ አፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ አምራችና አቅራቢ ለመሆን ብዛት ያላቸውን ምርቶች በማቅረብ ላይ ሲሆን፣ በኮሪደር ልማት የሚተከሉ የመብራት ፖሎችንና ሌሎች ግብዓቶችን በማቅረብ ይታወቃል፡፡
ድርጅቱ በቀጣይ ትልቅ የመስታወት ፋብሪካ በመገንባትና በማምረት በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሠራ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡
ምንጭ፡ ethiopianreporter


















