አትሌት እለተ-ሰንበት ግደይን ጨምሮ 9 እውቅ የሀገራችን አትሌቶች በከተማ እስተዳደሩ 500 ካሬ ሜትር መሬት ለመኖሪያ ቤት መገንቢያ በስጦታ ተበርክቶላቸው የነበረ ሲሆን ከግንባታ ጋር በተያያዘም ከመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ እና ከፕላን ልማት ቢሮ ጋር ተወያይተዋል።
አትሌቶቻችን ሀገር በውጥረት ውስጥ ሆና ስንደቅ ዓላማዋ በአለም አደባባይ ከፍ እንዲል ያደረጉ የሀገር መገለጫ ኩራቶቻችን ናቸው ያሉት የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢር ኃላፊ አቶ መኮንን ያዒ በከተማ አስተዳደሩ የተበረከተላቸሁ የመሬት ስጦታም በተሰማራችሁበት መስክ ለምታስመዘገቡት ድል ማትጊያ ነው ብለዋል።
በተበረከተላቸው መሬት የምትገነቡት የመኖሪያ ቤትም ለከተማዋ የሚመጥን ብቻ ሳይሆን ገጽታዋን የሚያጎላ እንደሚሆን ሙሉ እምነት አለኝ በማለትም አክለዋል።
ይህ እንዲሆን እንደ መሬት ነክ ተቋም በጋራ የሚጠበቅብንን በማድረግ ልንደግፋችሁና ልናገለግላችሁ ዝግጁ ነን ሲሉም ገልፀዋል።
በእኛ ዘረፍ ዓለም ሀገራችንን የምታውቀው በሩጫው ለሀገራችን በምናመጣው ድል ነው ያሉት አትሌቶቹ እናንተም ያንን ልፋታችንን ልፋታችሁ አድርጋችሁ ክብር ሰጥታቹን በከንቲባዋ የመሬት ስጦታ በእናንተ ደግሞ በዚህ ልክ መስተናገዳችን ኩራት ተስምቶናል ብለዋል።
በተሰጠን መሬት ባህር ማዶ የተመኘነውን ውብ የመኖሪያ መንደር በመፍጠር ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት እንፈጥራልን ሲሉም በተደረገላቸው መስተንግዶ መደሰታቸውን ገልፀዋል።


















