በሀገራችን የመጀመሪያው የሞርጌጅ ሪፋይናንስ ኩባንያ መንግስት 100 ቢሊዮን ብር ካፒታል በማስቀመጥ እና የአለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) 200 ሚሊዮን ዶላር በማበርከትብለማቋቋም መታሰቡን በዚህ ሳምንት መስማታችን ለሀገራችን የሪል እስቴት ዘርፍ ትልቅ ዕድል ነው።
በሪል እስቴት ኢንቨትመንት ውስጥ ካሉት ዋና ዋና ባለድርሻ አካላት መካከል መንግስት ፣ የካፒታል ማርኬት ( ገንዘብ አቅራቢ)፣ አልሚ፣ ቤት ገዢና ባለሙያዎች ይገኙበታል።
ወደ ሀገራችን የሪል እስቴት ዘርፍ ውስጥ በምንገባበት ወቅት ወቅታዊ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብ የቤት አቅርቦትን ለማስካት ያልተቻለው በሁሉም (አምስቱም) ባለድርሻ አካላት ምክንያት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በመንግስት በኩል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች በዘርፉ ውስጥ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት በተሻለ መጠን እየተወጣ መሆኑን አመላካች ነው። ለዚህም የመሬት አቅርቦት መሻሻል፣ የሪል እስቴት አዋጅ መጽደቅ (ስራ ላይ ባይውልም)፣ የውጭ ዜጎች ቤት እንዲገዙ የሚያችል አዋጅ ማጽደቁ፣ በአብሮ ማልማት ከባለ ሀብቴች ጋር አብሮ መስራቱ፣ የተለያዩ የቤት ግንባታ ፕሮግራሞችን መጀመሩ….መጥቀስ ይቻላል።
አሁን ሊመሰረት በእንቅስቃሴ ላይ ያለው የሞርጌጅ ሪፋይናንሲንግ ኩባንያ ምስረታም አንዱ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ይህ የሪፋይናንሲንግ ተቋም ባንኮች የረጅም ጊዜ ሞርጌጅ ብድር ለመስጠት ያለባቸውን የአቅም ውሱንነት መፍትሄ በመስጠት የረጅም ጊዜ ብድር እንዲሰጡ የሚያስችል ገንዘብ ያቀርባል ይህም ባንኮች በሪል እስቴት ዘርፍ ውስጥ አዳዲስ ብድሮችን እንዲሰጡ ያስችላቸዋል።
ይህም በዘርፉ ውስጥ ያለው ገንብቶ ለመሸጥ ከመቸገር ጋር ያለውን Liquidity Risk ያቃልላል፣ በርካታ ቤቶች እንዲገነቡ ያበረታታል፣ የገንዘብ አቅርቦት ሲሻሻል ከፍተኛ የሆነው የብድር ወለድ ይቀንሳል፣ ቤት ገዢዎች የተራዘመ የብድር መክፈያ ጊዜ ስለሚመቻችላቸው በየጊዜው የሚከፍሉት የብድር መመለሻ ገንዘን መጠን ይቀንስላቸዋል፣ በርካታ ብቃት ያላቸው አልሚዎች ወደ ዘርፉ እንዲቀላቀሉ ያነሳሳል፣ የውጭ ባለሀብቶችን ወደ በዘርፉ በመማብ ቀጥተኛ የሆነ የሚየውጭ ምንዛሪ ግኝት (FDI) ያሳድጋል ……
በተጨማሪም በሪፋይናንስ ብቁ ለመሆን የቤት መግዣና መገንቢያ ብድር አቅራቢዎች (ሞርጌጆች ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና IFC መስፈርቶችን ማሟላት ስላለባቸው ለብድር ብቁ ለመሆን አልሚዎች ወደ ትክክለኛ የመሬት ሰነድ እና የግንባታ ጥራት እንዲሄዱ ይገፋፋቸዋል። ይህም በዘርፉ ያለውን አለመተማመን ይቀንሳል።
ነገር ግን የሪል እስቴት ዘርፍ መሬት ስለቀረበ፣ የመገንቢያና የመግዣ ስለተመቻቸ ዘርፉ ስኬቱ ሙሉ አያደርገውም። ለቅኬታማነቱ የሚከተሉት እንደ ተግዳሮት ሊታዩ ይችላሉ:-
- የመሬት ሰነድ እና የህግ ችግሮች፦ የሪፋይናንስ ኩባንያ ግልጽ የመሬት ሰነድ ለሌላቸው ንብረቶች ሞርጌጅ መግዛት አይችልም። የመሬት ምዝገባ ስርዓት መዘግየት ለአልሚዎች ትልቅ እንቅፋት ሆኖ ይቀራል።
- የግንባታ ወጪ፦ ፋይናንስ ቢሻሻልም፣ ከውጭ የሚገቡ ብረት እና ማሽኖች ዋጋ በሎጂስቲክስ እና በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ከፍተኛ ሆኖ ይቀራል፣ ይህም የቤት ዋጋን ከፍ ያደርገዋል።
- የብቁነት መስፈርት፦ አልሚዎች በIFC የሚደገፈውን የቴክኒክ እና የአካባቢ ጥበቃ ጥብቅ መስፈርቶች ለማሟላት ሊቸገሩ ይችላሉ፣ በተለይም አነስተኛ የሀገር ውስጥ አልሚዎች ተጠቃሚ ለመሆን ይቸገራሉ።
- የመግዛት አቅም ገደብ፦ ከቤት ገዢዎች የሚጠበቀውን የረጅም ጊዜ ወርሃዊ ክፍያን ይቀንሳል፣ ነገር ግን አጠቃላይ የቤቱ ዋጋ (ዋና ገንዘብ + ወለድ) በእጅጉ ይጨምራል። ገዢዎች ይህንን ተረድተው ካልተዘጋጁ የገዢ ችግር ሊፈታ አይችልም።
- የቅድመ ክፍያ እንቅፋት፦ አብዛኛዎቹ ሞርጌጆች 20-30% የቅድመ ክፍያ ይጠይቃሉ። ለአማካይ የኢትዮጵያ ቤተሰብ ይህን መጠን መቆጠብ ትልቅ ተግዳሮት ነው።
- የገቢ ማረጋገጫ፦ መደበኛ የባንክ ዘርፍ የተረጋገጠ ገቢ ማረጋገጫ ይፈልጋል። ከፍተኛ የሆነው የኢትዮጵያ የስራ ኃይል ክፍል መደበኛ ባልሆነ ዘርፍ ውስጥ ስለሚገኝ፣ ለአዲሱ ብድር ብቁ ላይሆኑ ይችላሉ።
- የቤት መወረስ አደጋ፦ ረጅም የብድር ጊዜ ማለት ገዢዎች ለረጅም ጊዜ የተረጋገጠ አስተማማኝ ገቢን ይፈልጋል። ነገር የአገራችን ኡኮኖሚ ለመገመት ከሚከብድ የዋጋ ንረትና ለአንዳንድ ጊዜም ለስራ ማጣት የተጋለጡ ናቸው፣ ይህም ንብረታቸውን የማጣት ስጋት ሊያስከትል ይችላል።
ስለዚህ ይህ ጥሩ አጋጣሚ ወደ ዜጋ ጥቅም እንዲቀየር የሚከተሉት ትኩረት ቢዱረግባቸው መልካም ነው:-
፩)በመንግስት በኩል
- የዲጂታል መሬት ምዝገባ ማፋጠን፦ የተቋሙ ስኬት ግልጽ ሰነድ ላይ የተመሰረተ ነው።እየተከናወነ ያለውን የከተማ መሬት ምዝገባዎችን በዲጂታል ማፋጠን ለባንኮች አስፈላጊ ሰነዶችን በፍጥነት ማቅረብ።
- የተናጠል ካርታ አሰጣጥን ማፋጠን:- ከባንክ ብድር ጋር የተያያዙ ቤቶች ግብይት አንዱ ዋና ችግር በሚፈለገው መስፈርት መሰረት የግንባታው ዕርክፕን ለደረሰ ፕሮጀክት ተናጠል ካርታ ለመስጠት ያለው መዘግየት ነው።
- የፋይናንስ ትምህርት ማካሄድ፦ ለሪል እስቴት ግብይት ባለሙያዎችና ቤት ገዢዎች ስለ ረጅም ጊዜ ዕዳ አስተዳደር፣ የወለድ ስሌት እና የቤት ባለቤትነት ሃላፊነት ማስተማር ። ይህም ግብይቱ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ የወደፊት የዕዳ አለመክፈልንም የሚቀንስ ይሆናል።
- የውጭ ምንዛሬ ቅድሚያ ቢመቻች፦ ለገንቢዎችና የግንባታ ቁሳቁስ አስመጪዎችና አምራቾች ተደራሽ የሆነ የውጭ ምንዛሬ እንዲያገኙ መደረግ አለበት፤ አለበለዚያ “ተመጣጣኝ” የሚባል ዋጋ ስለማይኖር በአቅርቦት ወጪ ንረት ይሸረሸራል።
፪) የሪል እስቴት አልሚዎች፦
- በዲዛይን ደረጃ ካሉ ይልቅ የተገነቡ ቤቶችን ለገበያ ቢያቀርቡ ፦ ለግንባታ የሚሆን ብድር እስካገኙ ድረስ በዕቅድ ላይ ካሉ የ3D ህንጻ ይልቅ፣ የተጠናቀቁ ቤቶችን በመሸጥ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል።የቢዝነስ ሞዴላቸው ሊቀየር ይገባል።
- ወጪ ቆጣቢ ፕሬጀክቶችን መተግበር፦ የሚገነቧቸው ቤቶች ተበድሮ ገዢዎችን ለማስቻል ፕሮጀክቶቻቸውን ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ከሚገቡ ቁሳቁሶች ጥገኝነት በመቀነስ እና ዋጋን ለመቆጣጠር ፣ ዘመናዊ የግንባታ ቴክኒኮችን እና የሀገር ውስጥ ቁሳቁሶችን ቢጠቀሙ።
- ቀድመው ከባንኮች ጋር መስራት፦ ፕሮጀክቶቻቸው ለሪፋይናንስ ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ከአበዳሪ ባንኮች ጋር ቀድመው ይስሩ፣ የ የሚገነቧቸው ቤቶች “ለሞርጌጅ ዝግጁ” እንዲሆኑ ያደርጋል።
፫) ለቤት ገዢዎች፦
- ለቅድመ ክፍያ ይዘጋጁ፦ 20-30% የሚሆነውን የቅድመ ክፍያ ለማሰባሰብ በተለይ መቆጠብ ይጀምሩ።
- ገቢያቸውን መደበኛ ያድርጉ፦ የሀገራችን የግለሰብ ገቢ ግራ አጋቢ ነው። ጥቂት ሰው በወር ከሚከፈለው ገቢ በተጨማሪ ተጨማሪ ስራ በመስራት፣መደበኛ ያልሆኑ ስራዌችን በመስራት፣ ከውጭ ዘመድ በሚላክ ድጎማ ራሱን የሚያስተዳድር ስለሆነ ለአበዳሪ ባንኮች እውነተኛ ገቢውን አሳውቆ ለቤት መግዣ ብድር ብቁ ለመሆን ይቸገራል። በመሆኑም ሁሉንም ገቢዎችና የንግድ ግብይቶች በመዘገብ እና ግብርም በመክፈል የገቢ ታሪክ ቢገነቡ መልካም ነው።
- በባንኮች የሚቀርቡ የብድር ውሎችን ያወዳድሩ፦ የሪፋይናንስ ስርዓት እያደገ ሲሄድ፣ የተለያዩ ባንኮች የተለያዩ የወለድ ተመኖች ይሰጣሉ። ቤት ገዢዎችም የተሻለውን አመታዊ የወለድ ተመን (APR) ለማግኘት የባንክ ውሎችን ይመርምሩ ያወዳድሩ።
- አጠቃላይ ወጪን ይረዱ፦ ወርሃዊ ክፍያውን ብቻ ሳይሆን በ15 -20 ዓመት ውስጥ ሙሉ በሙሉ የሚከፍሉትን አጠቃላይ ገንዘብ አስሉ። ይህ ቤቱ በረጅም ጊዜ በእውነት ተመጣጣኝ መሆኑን ለማወቅ ይረዳል።
ስናጠቃልለው ይህ አዲስ ተቋም ለሀገራችን የቤቶች ገበያ ትልቅ እድል ነው። ነገር ግን ስኬቱ የሚወሰነው መንግስት፣ ባንኮች፣ አልሚዎች እና ገዢዎች በትብብር መስራታቸው ላይ ነው። ጥንቃቄ የተሞላበት እቅድ እና ትክክለኛ መረጃ ይህን ፕሮግራም ለሁሉም የሚጠቅም ማድረግ ይችላል።
















