የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በጋራ ያለሙት አዲስ የግንባታ ቁጥጥር መረጃ ስርዓት ይፋ ተደረጓል።
የኮንስትራክሽን ቁጥጥር መረጃ ስርዓቱን የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መስፍን ነገዎ(ዶ/ር) እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግሥት ሃሚድ ይፋ አድርገውታል። ይፋ የተደረገው የኮንስትራክሽን ቁጥጥር መረጃ ሥርዓት ግልፅነትና ተጠያቂነትን ማስፈን የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል።
የኮንስትራክሽን ቁጥጥር መረጃ ሥርዓቱ የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በቅርቡ ይፋ አድርጎ ወደ ተግባር የገባውን ሀገራዊ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢኒሼቲቭ መሠረት ተደርጎ የለማ ሥርዓት መሆኑ ተገልጿል።

ስርዓቱ በተበታተነ ሁኔታ እና በሰው ኃይል ይከናወን የነበረ የስራ ሂደትን ተናባቢ፣ የተዋሃደ፣ ወጥ እንዲሁም ዲጂታል ቴክኖሎጂ መር ወደ ሆነ አሰራር የማሳለጥ ዓላማ እንዳለውም ተመላክቷል።
የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በዚሁ ወቅት፤ የኮንስትራክሽን ቁጥጥር መረጃ ሥርዓት በዘርፉ የሚሰጠው አገልግሎት በጥራት፣ ውጤታማ በሆነ መንገድ ብሎም ስራዎችን ማዘመን የሚያስችል ነው ብለዋል።
በመላ ሀገሪቱ የሚከናወኑ የግንባታ ቁጥጥር ሂደቶችን ዘላቂ፣ የተሟላ፣ ግልጽ፣ ወጥ እና ወደ ተዋሃደ የዲጂታል አስተዳደር ስርዓት እንዲሸጋገር የሚያስችልም ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ግንባታዎችን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመው፤ ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸው አበርክቶም የላቀ እንዲሆን ያስችላል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መስፍን ነገዎ(ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ስርዓቱ ደህንነቱ የተጠበቀ የመረጃ ሥርዓት እንዲኖር የሚያስችል ነው ብለዋል።
የተቋሙን ቁልፍ ተግባራት በዲጂታል ስርዓት ማሳለጥ፣ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ማስፈን፣ መረጃን ማዕከላዊ ማድረግ፣ ዳታ መር የሆነ አስተዳደርን የማስፈን እንዲሁም ጤናማና ደህንነቱ የተረጋገጠ ስርዓት እውን በማድረግ ረገድ የላቀ ሚና እንደሚጫወትም ተናግረዋል።
ምንጭ፡ Ethiopian News Agency


















