ሀገራት የውስጥ ገቢያቸውን በተለያዩ መንገዶች የሚሞሉ ሲሆን ጎረቤታችን ኬንያ ከሀገር ውስጥ ገቢዋ 15 በመቶ ታክስ የምትሰበስበው ከንብረት ታክስ መሆኑ ይገለጻል፡፡
በኢትዮጵያ ግን ይህ መጠን 7 በመቶ ብቻ ሆኖ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በገንዘብ ሚኒስተር የታክስ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙላይ ወልዱ ከኢቢሲ ዳጉ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የንብረት ታክስ በየትኛውም ሀገር ያለና በእኛ ሀገር ግን የዘገየ መሆኑን ተናግረዋል።
ያደጉ ሀገራት 0.6 በመቶ የሀገር ውስጥ ገቢያቸውን ከንብረት ታክስ እንደሚሰበስቡ የተናገሩት ኃላፊው፤ ያላደጉ ሀገራት ደግሞ 0.3 በመቶ ገቢያቸውን ከዚህ ታክስ ይሰበስባሉ ብለዋል።
አሁን ሊጀመር የታቀደው የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅም በማይንቀሳቀስ መሬትና በቤት ላይ የሚውል ስለመሆኑ ኃላፊው ተናግረዋል።
ይህ ታክስ መሬቱም ቤቱም ዋጋ ያወጣው መንግሥት መሰረተ ልማት በማሟላቱ በመሆኑ ስለዚህ መንግሥት ላደረገው የሚከፈል ነው ብለዋል።
ይህ ታክስ 2 ሺህ እና ከዚያ በላይ ህዝብ በሚገኝባቸው ከተሞች ሁሉ የሚጣል ታክስ ሲሆን ይህ ማለት ግን የታክሱ አከፋፈል አንድ አይነት እንደማይሆን እና ምጣኔው በከተሞች ደረጃና በግለሰቦች የገንዘብ አቅም ላይ መሰረት ያደረገ እንደሚሆን ኃላፊው ገልጸዋል።
የዋጋ ንረት ባለበት በዚህ ወቅት ይህ ረቂቅ የታክስ አዋጅ ለመተግበር መታሰቡ ችግር ሊኖረው ይችላል ወይ ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄ አቶ ሙላይ ወልዱ በሰጡት ማብራሪያ፤ ይህ ታክስ የሚተገበረው ባለ ንብረት ላይ እንጂ አቅርቦት ላይ ባለመሆኑ ያለአግባብ በቤት ንብረት ላይ ያሉ ግዢዎችን ያስተካክላል ገበያውም እንዲረጋጋ ያደርጋል ብለዋል።
ከተሰጣቸው ጊዜ በላይ ታጥረው የተቀመጡ መሬቶችና ያልተከራዩ ቤቶች ላይ የሚጣለው መጠን ከፍተኛ በመሆኑ ለስራ የሚያበረታታ ይሆናል ሲሉም አክለዋል።
ይህ የንብረት ታክስ አዋጅ የጣራና ግድግዳ ታክስን የሚያካትት ሲሆን የኪራይ ገቢ ታክስን ግን አይጨምርም ነው ያሉት።
የንብረት ታክስ አዋጁ ንብረት ኑሯቸው ገንዘብ የሌላቸው የማህበረሰብ ክፍሎችን የክፍያ ሁኔታ የሚያጣጥም አሰራርም በውስጡ መያዙን አንስተዋል።
ለዚህም የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የከተማ ልማት ሚኒስቴር እና የገቢዎች ሚኒስቴር የተጣጣመ ፖሊሲ በማውጣት ክፍተት እንዳይፈጠር እየሰሩ ነው ሲሉ በገንዘብ ሚኒስቴር የታክስ መምርያ ሀላፊው አቶ ሙላይ ወልዱ ገልፀዋል።
ምንጭ፦ EBC


















