የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በመርካቶ ጣና ገበያ አካባቢ 2,500 ዘመናዊ የንግድ ሱቆች የሚገነቡበትን ታላቅ ፕሮጀክት በይፋ ያስጀመረ ሲሆን፣ በአዳራሽ ገበያ አካባቢ በ3 ወራት ውስጥ የተገነቡ 399 ሱቆችን አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ረሻድ ከማል በይፋ ባስጀመሩት በዚህ ፕሮጀክት፣ በጠቅላላ ስፋታቸው 1.8 ሄክታር በሆኑ 10 ሳይቶች ላይ ቀድሞ የነበሩትን 230 ሱቆች በመተካት ባለ 5 ወለል የሆኑ 2,500 ዘመናዊ የንግድ ሕንጻዎች የሚገነቡ ይሆናል።
የተነሱት ነጋዴዎች ከአንድ አመት በኋላ ግንባታው ሲጠናቀቅ እንደሚመለሱ መተማመኛ ውል ተዋውለዋል ።
በግንባታ ማስጀመሪያ ወቅት ዶ/ር ረሻድ ከማል ባደረጉት ንግግር ኮርፖሬሽኑ አገራዊ ለውጡን መነሻ በማድግ ባለፉት ዓመታት ባደረገው ጠንካራ ሪፎርም ዓመታዊ ገቢውን ከነበረበት 300 ሚሊዮን ብር ወደ 12.5 ቢሊዮን ብር በማሳደግ የጀመረውን ተቋማዊ ሪፎርም ማስቀጠል መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ከተከራይ ደንበኞችን በማሳመን እና የግል በለሀብቱን አሳታፊ የሚያደርግ አሰራር በመዘርጋት በርካታ የንግድ ሱቆችን ግንባታ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚሁ አሰራር ስልትም በዜሮ ኢንቨስትመንት በጠቅላላ ስፋታቸው 1.8 ሄክታር በሆኑ 10 ሳይቶች ላይ ባለ 5 ወለል የሆኑ እና 2,500 ዘመናዊ ሱቆችን የያዙ የንግድ ሕንጻዎች ግንባታ መጀመሩን ዶ/ር ረሻድ ከማል ተናግረዋል፡፡
ሰባት ኩባንያዎች አሥር ፕሮጀክቶችን ወስደው በራሳቸው 4.3 ቢሊዮን ብር ካፒታል በማፍሰስ 2,500 ሱቆችን ለመገንባት መሰማራታቸው ነው የተገለጸው።
ኮርፖሬሽኑ ብቁ ለሆኑና ከኮርፖሬሽኑ ጋር አብሮ ለመስራት ፍላጎት ላላቸው የግል አልሚዎች ከኮርፖሬሽኑ በጋር እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አዲስ የሚገነቡት የንግድ ሱቆች በአዲስ አበባ ከተማ ስታንዳርድ መሰረት ዘመናዊ የንግድ ሱቆች ሲሆኑ በቂ ፓርኪንግ ቦታቸውም ይዘው የሚገነቡ ይሆናል፡፡
ከዚህ ቀደም በነበሩት ቦታዎች ላይ የነበሩት ሱቆች 230 ብቻ የነበሩ ሲሆን፣ አሁን ወደ 2,500 በማደግ ለብዙ ሺዎች ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል። በትንሹ ከ10,000 በላይ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
እነዚህ የግንባታ ፕሮጀክቶች ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለአገልግሎት የሚበቁ ሲሆን፣ በከተማችን ለተጀመረው የኮሪደር ልማት እና የከተማ ገጽታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።
ለግንባታው ተብለው በፈረሱት ሱቆች ምክንያት ተቋሙ ቀድሞ የሚያገኘውን ገቢ እንዳያጣ ታሳቢ በማድረግም ተጨማሪ 399 ሱቆች በዚያው በመርካቶ አካባቢ በ3 ወራት ውስጥ ገንብቶ በማጠናቀቅ ወደ ኪራይ አገልግሎት ገብተዋል፡፡
ምንጭ፦ Federal Housing Corporation, WZ news
















