በአዲስ አበባ ከተማ በተለይም የጋራ መኖርያ ቤቶች፣ ሪልስቴቶች እና የማኅበር ቤቶች በብዛት በሚገኙባቸው የተለያዩ አካባቢዎች የተደራጁ ጫኝ እና አውራጆች ነዋሪዎችን ለእንግልት እና ምሬት ሲዳርጉ መቆየታቸው ተደጋግሞ ሲነገር ይሰማል።
ከባለቤቱ ፍላጎት ውጪ ማንኛውንም ዕቃ “እኛ ነን የምናወርደው” ማለት፣ ከፍ ያለ ዋጋ መጠየቅ እና መሰል ጉዳዮች የከተማዋ ነዋሪዎች ደጋግመው የሚያነሧቸው ችግሮች ናቸው።
ይሄንን ችግር ለማስቀረትም የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ አገልግሎት አሰጣጡን በሕግ እና ሥርዓት ለመከታተል እና ለመቆጣጠር ጫኝ እና አውራጅ ማኅበራትን መልሶ ከማደራጀት ባሻገር መመሪያ አውጥቶ ወደተግባር መግባቱ ይታወሳል።

ቢሮው በጫኝ እና አውራጅ ማኅበራት መመሪያ፣ በወንጀል መከላከል እና በሰላም እሴት ግንባታ ዙሪያ ከጫኝ እና አውራጆች ጋር ውይይት እያደረገ ይገኛል።
ጫኝ እና አውራጆች ከባለንብረቱ ፍላጎት ውጪ የማንኛውንም ሰው ዕቃ ማውረድም ይሁን ማጓጓዝ እንደማይችሉ እና ለእያንዳንዱ ዕቃ የዋጋ ተመን ስለመቀመጡ በውይይቱ ላይ ተነሥቷል።
ጫኝ እና አውራጆች ሕግ እና ሥርዓትን ብቻ ተከትለው ማገልገል እንዳለባቸውም ተመልክቷል።
አገልግሎታቸውን በሕግ እና ሥርዓት ብቻ ከማድረግ ባሻገር የአካባቢያቸውን ሰለም እና ፀጥታ በማስጠበቅ እንዲሁም በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመሳተፍ ከተማቸውን ማገልገል እንዳለባቸውም መጠየቁን አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ዘግቧል።
በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች 5 ሺህ 375 ነዋሪዎች በጫኝ እና አውራጅ ሥራ ተሰማርተው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸው ተጠቁሟል።
Source EBC


















