አቡቀለምሲስ ሪል እስቴት ማሰልጠኛ ተቋም በዛሬው ዕለት 125 የሪል እስቴት ሽያጭ ባለሙያዎችን አስመረቀ።
ከተመራቂዎች ውስጥ 60 የሚሆኑት በታዳሽ ኢንዱስትሪስ ኃ/የተ/የግ/ማ ሙሉ ክፍያቸው ተሸፍኖ የሰለጠኑ ሲሆን 15 ሰልጣኞች በተቋሙ ሙሉ ወጪያቸው እንደተሸፈነ ታውቋል።
ኢንጅነር ደሳለኝ ከበደ የአቡቀለምሲስ ሪል እስቴት ማሰልጠኛ ተቋም ባለቤትና ዋና ሥራአስኪያጅ እንደተናገሩት ተቋሙ በሪል እስቴት ዘርፍ የተለያዩ ስልጠናዎችን ለመስጠት በ2013 ዓ.ም የአቡቀለምሲስ ኮንስትራክሽን ኃ.የተ.የግል.ማ. እህት ተቋም ሆኖ የተመሰረተ ነው::

የስልጠና ተቋሙ ከተመሰረተበት ቀን አንስቶ በቀን፣ በማታና በቅዳሜና እሁድ መርሃ ግብሮች ሃያ ዙር ስልጠናዎችን የሰጠ ሲሆን ለተለያዩ የሪል እስቴት አልሚዎች እና ወደ ዘርፉ ለሚገቡ ኢንቨስተሮች የሪል እስቴት ኢንቨስትመንትና የግብይት ስልጠናዎችን ሰጥቷል።
ተቋሙ በሃያ ዙር መደበኛና ልዩ ስልጠናዎች ከስድስት መቶ በላይ ሰልጣኞችን ያሰለጠነ ሲሆን ከስልጠና በኋላና በስልጠና ወቅትም ከተለያዩ የሪል እስቴት አልሚዎችና የማርኬቲንግ ጥያቄዎች ወኪሎች በሚቀርቡለት ጥያቄ መሰረት ሰልጣኞች የስራ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ተደርጓል ብለዋል።
አያይዘውም “የተቋማችን ዋና አላማ በሪል እስቴት ዘርፍ ያለውን የሰለጠኑ ባለሙያዎች ፍላጎት ታሳቢ ያደረገና ለሰልጣኞች የሚፈጥረውን የስራ እድልና ጥሩ ገቢ ግምት ውስጥ ያስገባ በመሆኑ
ከትርፍ ይልቅ በተለያዩ ዘርፎች ተመርቀው ያለ ስራ የተቀመጡና በስራ ላይ ሆነው ተጨማሪ በመስራት ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ለሚፈልጉ ዜጎች መድረስ በመሆኑ መክፈል የሚችሉ በአነስተኛ ክፍያ እንዲማሩ በማድረግ ፣ የተወሰነ ክፍያ ከፍለው ቀሪ የስልጠና ክፍያቸውን
ሰልጥነው ሲጨርሱ ወይም ስራ ጀምረው የሚከፍሉበትን አማራጮችን በማመቻቸት፣ መክፈል ለማይችሉ ነጻ የስልጠና ዕድል በማመቻቸት ብዙዎችን ተደራሽ ለማድረግ ሞክሯል” ብለዋል።

ተቋማችን በተለያዩ ዙሮች ለሰለጠኑ ሰልጣኞች በአመት ሁለት ጊዜ የምረቃ መርሃግብር ያዘጋጃል: የምረቃ መርሃ ግብሮቹ ከምርቃት ባሻገር የስራ ትስስር የሚፈጠርባቸውና የተቋሙ ቀደምት ሰልጣኞችና በዘርፉ ስኬታማ የሚባሉ አንጋፋ ባለሙያዎችና የሽያጭ ተቋማት መሪዎች ልምድ የሚያካፍሉባቸው ውጤታማ መድረኮች ናቸው።
ተቋሙ የሚሰጣቸውን ስልጠናዎች ወደ አስራ አንድ ከፍ ያደረገ ሲሆን ተጨማሪ የማሰልጠኛ ክፍሎችን በማስፋት በዚህ ዓመት በሪል እስቴት ዘርፍ ክፍተት ያለባቸውን ልዩ ልዩ አጫጭር ስልጠናዎችን ለመስጠት ዝግጅቱን አጠናቋል።
በዛሬው ዕለት የሚመረቁ ሰልጣኞቻችንና ከዚህ ቀደም በተቋማችን የሰለጠኑ ሰልጣኞቻችን ብዙዎቹን አዳዲሶቹን ስልጠናዎቻችን በነጻና አንዳንዶቹን በአነስተኛ ክፍያ እንዲሰለጥኑ የሚደረግ ሲሆን ሌሎች ፍላጎት ያላቸው በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች በተመጣጣኝ ክፍያ የስልጠናው ተካፋይ እንዲሆኑ ይደረጋል።
(በድሬቲዩብ ሪፖርተር)


















