ኖህ ሪል እስቴት በከተማዋ ስልታዊ ቦታዎች ላይ የገነባቸውንና ለነዋሪዎች ምቹ የሆኑ ግዙፍ የመኖሪያና የንግድ መንደሮችን በይፋ መርቆ ለደንበኞቹ አስረከበ።
ኩባንያው ግንቦት 1 ቀን ባካሄደው ደማቅ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት፣ በኖህ አስኳል (እንቁላል ፋብሪካ) እና በኖህ ቪክቶሪ (ሴቶች አደባባይ) የጋራ መኖሪያ መንደሮች የገነባቸውን በድምሩ 1,341 የመኖሪያ ቤቶች እና የንግድ ሱቆች ቁልፍ ለባለቤቶቻቸው በይፋ አስረክቧል።
ይህ ክንውን የአዲስ አበባን የቤት ፍላጎት ለማቃለልና የከተማዋን ገጽታ ለመቀየር እየተደረገ ላለው ጥረት ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው ተገልጿል።
በምረቃው መርሃ ግብር ላይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስኪያጅ ክቡር ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፣ የኖህ ሪል እስቴት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ዘሪሁን፣ የኩባንያው የቦርድ አባላት፣ አዲሶቹ የቤት ባለቤቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች ተገኝተዋል።
በዕለቱ ንግግር ያደረጉት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ መርሃ ግብሩ ከመደበኛ የቁልፍ ርክክብ ባለፈ በአዲሶቹ ነዋሪዎች መካከል ጠንካራ የማህበረሰብ ትስስር እንዲፈጠር የሚያደርግ ታሪካዊ ዕለት መሆኑን ገልጸዋል።
የኖህ ሪል እስቴት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ዘሪሁን፣ ደንበኞቻቸው የለፉበትንና የጠበቁትን የቤት ቁልፍ በእጃቸው ሲያስገቡ በማየታቸው ታላቅ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጾ፤ ለአዲሶቹ ባለቤቶች በአዲሱ መኖሪያቸው የተቃና እና የተደሰተ የኑሮ ዘመን እንዲሆንላቸው መልካም ምኞቱን አስተላልፏል።
ምንጭ: Noah Real Estate


















