በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እና የሪል እስቴት ሥራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው ሴንቸሪ ኢንቨስትመንት ግሩፕ (Century Investment Group) ተወዳጁን ድምፃዊ ዳዊት ጽጌን የሴንቸሪ ሪል እስቴት ይፋዊ የብራንድ አምባሳደር አድርጎ መሾሙን በትላንትናው ዕለት አስታወቀ።
ድርጅቱ ይህንን አዲስ አጋርነት ይፋ ያደረገው የረጅም ጊዜ የልማት ተሳትፎውን እና የንግድ እንቅስቃሴውን ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር ያለመ እንቅስቃሴ አካል እንደሆነ ገልጿል።
ከድርጅቱ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የፊርማ ሥነ-ሥርዓት የተከናወነ ሲሆን፣ በወቅቱም የአርቲስቱ የሙያ አጋር አበጋዝ ሺኦታ፣ ከፍተኛ የመንግስት አካላት፣ የቦርድ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች ተገኝተዋል።

ስምምነቱ “ደሞ በዚህ ላይ… ሥራዎቻችን ምስክሮቻችን!” በሚል አዲስ የቅስቀሳ ዘመቻ ስር የተከናወነ መሆኑን የገለጹት የድርጅቱ የቦርድ አማካሪ አቶ አበበ ድንቁ፣ ሴንቸሪ ሪል እስቴት በዘርፉ በቆየባቸው 10 ዓመታት በአዲስ አበባ እና አካባቢው በ16 ቁልፍ ቦታዎች ላይ ለንግድ፣ ለቢሮ እና ለመኖሪያ የሚሆኑ ሕንፃዎችን በመገንባት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህ የቅስቀሳ ዘመቻ ድምፃዊ ዳዊት ጽጌ ከድርጅቱ ጋር በመተባበር በህብረተሰቡ ዘንድ ሰፊ ተደራሽነት ያላቸውን ስራዎች እና የብራንድ እንቅስቃሴዎችን ይፋ እንደሚያደርግ ተመላክቷል።
ላለፉት 70 ዓመታት በስኬታማ የንግድ ስራ ዘርፍ፣ ከ30 ዓመታት በላይ በኢንዱስትሪው ዘርፍ፣ እንዲሁም ባለፉት 10 ዓመታት አዲስ አበባን መሰረት አድርጎ ዘመናዊና ምቹ ህንፃዎችን በመገንባት በዘርፉ ያለውን ድርሻ ማጎልበቱን ድርጅቱ ገልጿል።
ተጠናቀው ለአገልግሎት የበቁት ፕሮጀክቶች በቦሌ መድኃኒያለም የሚገኘው ሴንቸሪ ራዲያንስ አፓርትመንት፣ በቦሌ ብራስ የሚገኘው ሴንቸሪ አዲስ ትሬዠር አፓርትመንት፣ በቦሌ አትላስ የሚገኘው ሴንቸሪ ሼባ ሆምስ፣ በካሳንቺስ የሚገኘው ሴንቸሪ ሴንትራል አፓርትመንት፣ በተክለሃይማኖት የሚገኘው አስመን ተክለሃይማኖት፣ ከሴንቸሪ ኤክስክሉሲቭ ታወር ጀርባ የሚገኘው ኤስ ኤች ጂ እንዲሁም በቦሌ ቡልቡላ 93 ማዞሪያ የሚገኘው ኦክ አፓርትመንት ይገኙበታል።
በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ ሜክሲኮ ቫልዩ፣ ሴንቸሪ ኦሎምፒያ፣ ሜጋ ፒኮክ፣ ቦሌ ሰላም መንገድ እና ታይስ አዋሬ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ሙሉ በሙሉ በግንባታ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

ከንግድና ከሪል እስቴት ልማት ስራው ባሻገር ድርጅቱ በማህበራዊ ኃላፊነት ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ አርአያነቱን በተግባር ማስመሰክሩ የተገለፀ ሲሆን፣
ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ከ2,000 በላይ ተማሪዎችን በትምህርት ቁሳቁስ መደገፉን፣ በየካ ክፍለ ከተማ የምግብ ማዕከል በመገንባት በየቀኑ ለ250+ ወገኖች የምግብ አገልግሎት መስጠቱን፣ ከ500 በላይ አረጋውያንን በየወሩ በቋሚነት መርዳቱን እና በአዲስ አበባና በቢሾፍቱ ከተሞች ከ50 በላይ አዳዲስ ቤቶችን ገንብቶ ማስረከቡን ጠቅሷል።
በተጨማሪም ድርጅቱ እንደ “ገበታ ለትውልድ”፣ “ገበታ ለሀገር”፣ “አረንጓዴ አሻራ” እና የኮሪደር ልማት ባሉ ሀገራዊ እና ብሄራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ በግንባር ቀደምትነት በመሳተፍ አጋርነቱን ማሳየቱ ተመላክቷል።
ይህ ከድምፃዊ ዳዊት ጽጌ ጋር የተደረገው አዲስ ትብብርም የድርጅቱን የቆየ ስም፣ ጥራት እና እሴት ከህዝብ ጋር የበለጠ የሚያቀራርብና በቀጣይ የሚከናወኑ የሪል እስቴት ፕሮጀክቶችን በጉጉት እንዲጠበቁ የሚያደርግ እንደሆነ ተገልጿል።


















