ጊፍት ሪል እስቴት የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ ለመቄዶንያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የቁሳቁስ ድጋፍ በዛሬው እለት አድርጓል።
በመርሀገብሩ የጊፍት ቢዝነስ ግሩኘ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች የተገኙ ሲሆን በዛሬው እለት የተደረገው የቁሳቁስ ድጋፍም የዘይት የፍራሽና የበሬ ድጋፍ ነው።
በድጋፍ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙትና ድጋፉን ያበረከቱት የጊፍት ቢዝነስ ግሩፕ መስራችና ባለቤት አቶ ገ/የሱስ ኢጋታ፤ መቄዶንያ የአረጋዊያንና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል በሺዎች ለሚቆጠሩ የሀገር ባለውለታ አረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን ለሚያደርገው ያልተቆጠበ እንክብካቤ፤ ጊፍት ቢዝነስ ግሩፕ በየጊዜው ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በቀጣይም ማዕከሉ ተደራሽነቱን ለማስፋት በሚያደርጋቸዉ እንቅስቃሴዎች ቢዝነስ ግሩፑ የበኩሉን ኃላፊነት እንደሚወጣ ተናግረዋል።
ጊፍት ቢዝነስ ግሩፕ ለማዕከሉ እያደረገ ስለሚገኘው ድጋፍ ምስጋና በማቅረብ ወደፊትም ድጋፉን እንደሚቀጥል በማሳሰብ መስከረም 15 የጊፍት ቢዝነስ ግሩፕ በመቄዶንያ የስጦታ ቀን ሆኖ መሰየሙን አብስረዋል፡፡
የማዕከሉ መስራችና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ቢንያም በለጠ በበኩላቸዉ መቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ራሳቸውን ችለው መታከም የማይችሉና የአልጋ ቁራኛ የሆኑ ህሙማንን በማንሳት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ጊፍት ቢዝነስ ግሩፕ የዛሬ ዓመት 13 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ባለሁለት መኝታ አፓርትመንትና 3.5 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የበዓል ስጦታ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ድርጅቱ የደንበኞችን ፍላጎትና ከጊዜው ጋር ተመራጭ የሆነ ዲዛይንና አዳዲስ እሴቶችን በማካተት ከዚህ ቀደም ዘመናዊ መንደሮችን ገንብቶ ለተጠቃሚዎች ማስተላለፉ ተገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት ደግሞ በለገሃር፣ በተክለ ሀይማኖት፣ በ22 ማዞሪያ፣ በሲ ኤም ሲ እና በፈረስ ቤት ዘመናዊ፣ ቅንጡ የመኖሪያና የንግድ አፓርትማ መንደሮች እየገነባ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡
በመንደሮቹ ትምህርት ቤቶች፣ የህክምና ተቋማት፣ ሞሎች፣ የመዝናኛ ስፍራዎች ከበቂ የመኪና ማቆሚያ ጋር ተካተዋል ተብሏል፡፡
ጊፍት ሪል እስቴት በጊፍት ቢዝነስ ግሩፕ ውስጥ በ2005 ዓ.ም የተቋቋመ እና ምቹ እና የቅንጦት አኗኗር የሚያራምዱ ዘመናዊ መገልገያዎችን ያሟሉ ምቹ ቤቶችን የመስራት ተልዕኮ አንግቦ የተቋቋመ ኩባንያ ነው።
ምንጭ፡ ድሬትዩብ፣ ጊፍት ቢዝነስ ግሩፕ


















