ኦቪድ ቤቶች ባንክ አክሲዮን ማህበር ወደስራ ሊያስገባው የሚያስችለውን የአክሲዮን ሽያጭ በስካይላይት ሆቴል ባካሄደው መርሃ ግብር አስጀምሯል።
ባንኩ 20 ቢሊዮን ብር ካፒታል ለማሰባሰብ የሚረዳውን የ20 ሚሊዮን የአክሲዮን ሽያጭ ያቀረበ ሲሆን የአክሲዮን ሽያጩ ሥራ እንዲጀምር የሚያስፈልገውን ካፒታል ለማሰባሰብ የሚረዳው መሆኑ ተገልጿል።
ከአክስዮን ሽያጭ የሚሰበሰበው ገንዘብ ባንኩ በመላው ኢትዮጵያ የቤትና የቤት ብድር አቅርቦትን የማስፋፋት ተልዕኮውን እንዲወጣ ያስችለዋል ተብሏል።

የባንኩ ዝቅተኛ የግለሰብ አክሲዮን ግዥ 200,000 ብር ፣ ከፍተኛው 1 ቢሊዮን ብር መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ሥራ ለመጀመር 5 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የሚያስፈልገው እንደሆነ ተገልጿል።
ኦቪድ ኮንስትራክሽን በአዲስ አበባ ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ 60,000 ቤቶችን ለማልማት ያቀደ ሲሆን ባንኩ እቅዱን ለማሳካት ትልቅ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል።

የቤቶቹ ግንባታ 450 ቢሊዮን ብር ይፈጃል የተባለ ሲሆን በኦቪድ ኮንስትራክሽንና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ70፡30 የሽርክና ስምምነት መሰረት የሚገነባ መሆኑ ተጠቁሟል።
የከተማ አስተዳደሩ በቦሌ ቡልቡላ አካባቢ ለልማት የሚውል 460 ሄክታር የሚጠጋ መሬት ማዘጋጀቱም ነው የተገለፀው።














