ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ በእኛ ተቋም የሚሰለጥኑ የሽያጭ ባለሙያዎችን ቀጥረው የሚያሰሩ የሪል እስቴት አልሚና ሽያጭ ወኪል ተቋማት የማያቋርጥ የሰው ሃይል ጥያቄ መንስዔን ስናጠና የደረስንበት ክፍተትን በመንተራስ የሌሎች ሀገራትንም ከዘርፍ የማቋረጥ ምጣኔንና ምክንያት ካገናዘብን በኋላ ብናጋራው ሊጠቅም ይችላል ብለን በማሰብ ነው።
በሀገራችንና በአለም አቀፍ ደረጃ የሪል እስቴት ግብይት ባለሙያዎች (ኤጀንቶች) በዘርፉ የማይቆዩበት ምክንያት፣ የውጭ ሀገራት ተሞክሮ እና የማቋረጥ ምጣኔ (Turnover Rate) በአጭሩ ተጠቃሎ እንደሚከተለው ሊቀርብ ይችላል፦
ሀ. ባለሙያዎቹ የማይቆዩባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች
- የፋይናንስ አለመረጋጋት፦ ቋሚ ደሞዝ አለመኖር፣ የባንክ ብድር ዕጥረት እና ቤት ለመሸጥ ረጅም ወራት መፍጀቱ።
- የኮሚሽን መከልከል፦ አልሚዎች ወይም ገዥና ሻጭ ውል ካጠናቀቁ በኋላ የባለሙያውን ክፍያ ማዘግይፕት ቆራርጦ መክፈል እንዲሁም መከልከላቸው።
- የመረጃ እጥረት፦ የትኛው ቤት በምን ያህል ዋጋ እንደሚሸጥ የሚያሳይ ማዕከላዊ የዲጂታል መረጃ ቋት (MLS) አለመኖሩ።
- ህገ-ወጥ ውድድር፦ ማንም ሰው ያለ ፈቃድና ስልጠና “ደላላ” መሆን መቻሉ እና የሙያው ክብር ዝቅ ማለት።
ለ. የአለም አቀፍ የማቋረጥ ምጣኔ (Turnover Rate) በመቶኛ
- አሜሪካ፦ ወደ ዘርፉ በገቡ በአንደኛው አመት 75%፣ በ5 አመት ውስጥ 87% ኤጀንቶች ስራውን ይተዋሉ።
- ዱባይ፦ በመጀመሪያው አመት 80% ያቋርጣሉ (በከፍተኛ ውድድር እና መጀመሪያ ላይ ገቢ በማጣት)።
- ኬንያ፦ አመታዊ የማቋረጥ ምጣኔ ከ30% – 40% ይደርሳል (ባልተመዘገቡ ደላላዎች ውድድር ምክንያት)።
- ኢትዮጵያ፦ ይፋዊ መረጃ ባይኖርም የማቋረጥ ምጣኔው ከ85% በላይ እንደሚሆን ይገመታል።
ሐ. ለእኛ ግብይት ከሚቀርቡ ከሌሎች ሀገራት (ዱባይ እና ኬንያ) ምን እንማራለን?
- የመረጃ ግልጽነት (ዱባይ)፦ በስማርት መተግበሪያ (Dubai REST) እያንዳንዱ ቤት እና ኤጀንት በቀላሉ ይረጋገጣሉ።
- የክፍያ ዋስትና (ዱባይ/ኬንያ)፦ የኮሚሽን ገንዘብ በገለልተኛ የባንክ ሂሳብ (Escrow Account) በህግ ይጠበቃል።
- የሙያ ማህበር ጥበቃ (ኬንያ)፦ በህግ የተቋቋመው ማህበር (EARB) የባለሙያዎችን መብት ያስከብራል።
መ. ከሌሎች ሀገራት የእኛን የማቋረጥ ምጣኔ ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ታሳቢዎች:-
- ዘርፉን ሳያውቁ መግባት፦ የሪል እስቴት አልሚዎችና የሽያጭ ወኪል ተቋማት የሽያጭ ባለሙያዎችን ወደ ግብይት ሲያስገቡ አሻሻጥን እንጂ ዘርፉን እንዲያውቁ አያደርጓቸውም። አጣድፈው ያስገቧቸዋል ተጣድፈው ይወጣሉ/ አጣድፈው ያባርሯቸዋል። ዘርፉን ያወቁ ረዘም ባለ ልፋት ስኬት እንደሚገኝ ይረዳሉ በትዕግስት ጠብቀው ስኬታማ ይሆናሉ።
- ወጥ የሆነ የስልጠና አለመኖር:- ብዙ የሪል እስቴት ተቋማት ባለሙያዎቻቸውን የተለያዩ ስልጠናዎችን ይሰጣሉ። ብዙዎቹ የማነቃቃት “ትችላለህ: ትችያለሽ” ዓይነት ስልጠናዎች ፣ አንዳንዶች የሽያጭ ስራ ላይ ያተኮሩ፣ ብዙዎች ከሀገራችን ውጪ የሚሰጡ ስልጠናዎችን በአሰልጣኝ ወይም በዩቲዩብ እንዲመለከቱ በማድረግ በተዘበራረቀ ስልጠና ተመሳሳይ ስራ ላይ እንዲገቡ መደረጉ
- የክፍያ ሁኔታ:- ክፍያው አነስተኛ ደመወዝና ከፍ ያለ ኮሚሽን ላይ የተመሰረተ ቢሆንም በሚከፈለው ደመወዝ ረክቶ መቀመጥ
- እቅድ አለሟሟላት:- ለቅጥር የሚቀመጠውን ዝቅተኛ የሶስት ወር አፈጻጸም እቅድ ለማሟላት ባለመቻል
- ዘርፉን በልዩነት የሚመራው አካል አለመኖር:-የሪል እስቴት ዘርፍ ከፍተኛ ሙዓለ-ነዋይ የሚዘዋወርበት በመሆኑ በርካቶችን ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ይስባል።ለዘርፉ ጤና ሲባል ብዙ ሃገራት ዘርፉን የሚመሩበት መመሪያ አዘጋጅተው፣ ዘርፉን የሚመራ አካል ሰይመው ወደ ዘርፉ የሚቀላቀሉ በሙሉ ሃላፊነትና ተጠያቂነት እንዲኖራቸው ጭምር መስፈርት ያስቀምጣሉ። በሀገራችን ይህንን የሚመራው አካል ባለመኖሩ ከተጎዳው የዘርፉ ተዋናዮች ውስጥ የግብይት ባለሙያዎች ይገኙበታል ። ያለ በቂ ስልጠና እንዲገቡ፣ ዘርፉን ሳያውቁ እንዲገቡ፣ በተገቢው መንገድ ክፍያ እንዳያገኙ፣መብትና ግዴታቸውን እንዳያውቁ….በማድረግ ከዘርፋ እንዲወጡ ያደርጋቸዋል ….
ሠ. መፍትሄዎቹ :-
ከመፍትሄዎቹ አንዱ መመሪያና መሪ እንዲኖር ማድረግ ነው። ለዚህም አዲሱ የኢትዮጵያ የሪል እስቴት አዋጅ የተወሱኑ መፍትሄዎች አስቀምጧል። ይህ አዋጅ ወደ ትግበራ ገብቶ የሚመራው አካል ቢሰየም የሚከተሉትን በማስፈጸም በጎ አስተዋጽኦ ያደርጋል ….
- የፈቃድ ግዴታ፦ ያለ ሙያ ብቃት ማረጋገጫ (Certificate of Competence) መስራት በህግ ያስቀጣል።
- የውል ግዴታ፦ የኮሚሽን መጠን እና አከፋፈል በፅሁፍ ውል መታሰር እንዳለበት ያስገድዳል።
- የደረጃ ክፍፍል፦ እንደ ባለሙያዎቹ እውቀት፣ ካፒታል እና ልምድ ደረጃ (Grade) ይሰጣል።
ባጭሩ በአለም ዙሪያ መጀመርያ ላይ ያለ ሽያጭ የሚቆዩበት የ9-14 ወራት የገንዘብ ክምችት (Financial Runway) የሌላቸው ኤጀንቶች በፍጥነት ይወጣሉ። አዲሱ የኢትዮጵያ አዋጅ በተግባር ሲተረጎም ግን ዘርፉን እንደ ዱባይ እና ኬንያ ስልታዊ በማድረግ ባለሙያዎች በስራቸው ላይ እንዲቆዩ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል።


















