አርኪ ኤቨንት ኦርጋናይዘር ለስድስተኛ ጊዜ የሚያዘጋጀው “የአርኪ የሪል ስቴት የቤቶች እና የሱቅ ሽያጭ ኤክስፖ” ዛሬ መስከረም 8 ቀን 2019 ዓ.ም በጊዮን ሆቴል በታላቅ ድምቀት ተከፈተ።
እስከ መስከረም 10 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ ለተከታታይ ቀናት የሚቆየው ይህ ኤክስፖ “አዲስ ዓመት አዲስ ቤት” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ሲሆን፣ በከተማዋ የሚገኙ የሪል ስቴት ቤቶች እና የሱቅ ገዢዎችን ከሻጮች ጋር የሚያገናኝ ሰፊ መድረክ እንደሆነ ተገልጿል።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የአርኪ ኤቨንት ኦርጋናይዘር ባለቤት እና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ ግርማ ኤክስፖው በዘርፉ ጤናማ የቤት ግብይት እንዲኖር ዓላማ አድርጎ የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም የሪል ስቴት ተቋማት ለደንበኞቻቸው በገቡት ቃል መሠረት ቤቶችን ገንብተው እንዲያስረክቡ ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም አዘጋጅ ተቋሙ በኤክስፖው ወቅት ለሽያጭ ሠራተኞች የሚሆን ልዩ የማበረታቻ ሽልማት ማዘጋጀቱን አስታውቋል።
በዚህም መሠረት የሽያጭ ሠራተኞች ኤክስፖውን የሚያስተዋውቅ ተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዮ) በቲክቶክ (TikTok) ማህበራዊ ገጻቸው ላይ በማጋራት፣ 100ሺ እይታ (Views) እና 10ሺ «ላይክ» ማግኘት ከቻሉ ከ50 ሺህ ብር ጀምሮ ሽልማት እንደሚበረከትላቸው ተገልጿል።

















