ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የአዲስ ቱሞሮ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ግንባታ ማስጀመሪያ ዝግጅት በአዲስ አበባ ጎተራ አካባቢ ተካሄደ።
በ35 ሄክታር መሬት ላይ ከቻይናው “CCCC” ጋር በመተባበር የሚገነባው ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በከተማ ውስጥ አዲስ ከተማን የመገንባት ያህል ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
የኢኮኖሚ ዞኑ በውስጡ ትላልቅ ሞሎችን፣ የመኖሪያ አፓርትመንቶችን፣ ቢሮዎችን፣ የትምህርት እና የጤና ተቋማትን እንዲሁም ሰፋፊ መዝናኛዎችንና የውሃ አካላትን እንዲሁም የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላትን ያካተተ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አዲሱ የኢኮኖሚ ዞን ለመዲናዋ አዲስ ገፅታ የሚያላብስ፣ ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነቷን የሚያጎላ፣ ተጨማሪ የውበት ምንጭ የሚሆን፣ ለነዋሪዎች ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥር እና ንግድን የሚያሳልጥ ትልቅ ዓለም አቀፍ የግብይት ማዕከል ይሆናል ብለዋል፡፡በተጨማሪም ኢኮኖሚ ዞኑ ማህበራዊ አገልግሎቶችን የሚሰጡ መሰረተ ልማቶችን ያካተተ ሲሆን ፥ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ወደ ስራ እንደሚገባ ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ገልጸዋል።

















