ለመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በእጅጉ ተጋላጭ በሆነችው ጃፓን መሐንዲሶች አዲስ እና አስደናቂ ቴክኖሎጂን በመሞከር ላይ ይገኛሉ።
በ “Air Danshin Systems” የተገነባው ይህ ቴክኖሎጂ የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት በሚከሰትበት ጊዜ የመኖሪያ ቤቶች ከምድር ላይ ተነስተው እንዲንሳፈፉ የሚያደርግ ነው።
የዚህ ቴክኖሎጂ አሰራር በሴንሰሮች ታግዞ የሚሰራ ሲሆን የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት ሲጀምር ሴንሰሮቹ ወዲያውኑ ምልክት ይሰጣሉ። ያን ጊዜ የአየር መጭመቂያዎች ከቤቱ በታች ከፍተኛ የአየር ግፊት በመፍጠር ቤቱ ከመሠረቱ ላይ ለጥቂት ሳንቲሜትሮች ተነስቶ በአየር ላይ እንዲንሳፈፍ ያደርጋሉ።
ይህ ሂደት ቤቱ ከመሬቱ ንዝረት ጋር እንዳይገናኝ በማድረግ ከከባድ ጉዳት የሚጠብቀው ሲሆን የመሬት መንቀጥቀጡ ሲቆም ወይም መሬቱ ሲረጋጋ ቤቱ ቀስ ብሎ ወደ መሠረቱ ይመለሳል።
ይህ ፈጠራ በተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ በሚያጋጥማቸው አካባቢዎች የሰዎችን ህይወት እና ንብረት ለመታደግ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል።


















