ባማኮን ሪል እስቴት በቦሌ አዉሮፕላን ማረፊያ አካባቢ የገነባውንና ግንባታው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀውን ዘመናዊ የመኖሪያ አፓርታማ ህንፃ በዛሬዉ እለት በይፋ መርቆ ለደንበኞቹ አስረከበ።
ፕሮጀክቱ በሀገሪቱ የታየውን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና እና የህንጻ መገንቢያ ቁሳቁሶች ዋጋ ንረት ተቋቁሞ፣ በደንበኞች ላይ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ክፍያ ሳይጠይቅ መረከቡ ተገልጿል።
የባማኮን ሪል እስቴት የሽያጭና ማርኬቲንግ ዋና ኦፊሰር አቶ ፍሬው በየነ በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደገለጹት፤ ህንፃው በአጠቃላይ 22 ሰፋፊ መኖሪያ ቤቶችን እና ተጨማሪ አንድ የፔንት ሃውስ (Penthouse) መኖሪያን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።
ህንፃው በየወለሉ (per floor) ሁለት አፓርታማዎችን ብቻ የያዘ ሲሆን፣ ይህም ቤቶቹ ሰፋፊ፣ ዘመናዊና ምቹ እንዲሆኑ ታስቦ የተገነባ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንዲሁም በየወለሉ ላይ የሚገኙት “A” እና “B” የተሰኙት ቤቶች 206 እና 208 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው ሲሆን፣ ለነዋሪዎች አስተማማኝ ፀጥታና ግላዊነትን (Privacy) የሚያጎናጽፉ የቅንጦት (Super Luxury) መኖሪያዎች መሆናቸው ተብራርቷል።

በተጨማሪም ቤቶቹ ዘመናዊ (Modern) እና የሀገር ውስጥ ባህላዊ ምግቦችን ለማዘጋጀት የሚረዳ (Traditional) ባለሁለት ኩሽናን ያካተቱ ሲሆን፣ ይህም የምግብ ሽታና ጭስ ወደ ሳሎን እንዳይሰራጭ ታስቦ የተሰራ ነው።
በሀገሪቱ የነበረው የገንዘብ ምንዛሬ ለውጥ (Devaluation)፣ የጦርነት ተፅዕኖ እና የነዳጅ ዋጋ መጨመር በህንፃ መገንቢያ ግብአቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ቢያስከትልም፤ ኩባንያው ደንበኞቹን ከተጨማሪ ክፍያ በጠበቀ መልኩ ቤቶቹን ማስረከብ መቻሉን የሥራ ኃላፊው ገልጸዋል።
በተጨማሪም ባማኮን በአጠቃላይ ስምንት እህት ኩባንያዎች ያሉት ሲሆን፣ እነዚህ ኩባንያዎች እርስ በርስ የሚደጋገፉበት ጠንካራ አቅም መኖሩ ሥራው ሳይስተጓጎል እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን ገልጸዋል።
“ህንፃው ወደ ሽያጭ ከመውጣቱ በፊት ከ80% እስከ 85% የሚሆነው ግንባታው ተጠናቆ እንደነበር የተጠቀሰ ሲሆን ይህም በደንበኞች ላይ ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ ሳይደረግ ሙሉ በሙሉ አጠናቀዉ (Fully Finished) ለማስረከብ መቻላቸዉንም ገልፀዋል።
ከዚ ቀደም በካዛንችስ ፣ ባምቢስ አትላስ፣ፍሬንድሺፕ ፓርክ፣ቦሌ ኤርፖርት ቪው ፣በሜክሲኮ እና ቡልቡላ ሳይቶች ላይ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ግንባታዎችን አጠናቆ ለደንበኞች ማስረከቡ ተገልጿል።
ባማኮን ሪል እስቴት ከተቋቋመ ሰባት ዓመታት የሆነው ሲሆን፣ አሁን ያስረከበው ህንፃ አራተኛ ፕሮጀክቱ ነው። ዋናው እናት ኩባንያ የሆነው ባማኮን ኢንጂነሪንግ በአዲስ አበባ የባንክ ዲስትሪክት አካባቢ በርካታ ግዙፍ ህንፃዎችን በመገንባት የሚታወቅና በዘርፉ ከ23 ዓመታት በላይ ልምድ ያለው ታላቅ ኩባንያ መሆኑ ይታወቃል።
ምንጭ: ethiofm, Fastmereja


















