የኦቪድ ሆልዲንግስ የሠራተኞች ቀን መርሃ ግብር ከ1500 በላይ ሠራተኞች በተገኙበት ባለፈው ሐሙስ መስከረም 21 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል በድምቀት ተከናውኗል።
“የተናበበ ስትራቴጂ፣ አመራር፣ የሰው ኃይል እና አፈጻጸም” በሚል መርህ የኩባንያው ከፍተኛ አመራሮች፣ የቦርድ ተወካዮች፣ የእህት ኩባንያዎች የስራ ሃላፊዎችና የኩባንያው ሠራተኞች በተገኙበት በተካሄደው በዚህ መርሃ ግብር፤ “ኖርዝ ስታር – North Star” (መሪ ኮከብ) የተሰኘው የተቋሙ አዲስ ስትራቴጂ እና የቀጣይ አምስት አመታት ስትራቴጂክ ዕቅድም ይፋ ተደርጓል።
የኦቪድ ሆልዲንግስ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ ታደሰ በመርሃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ መላው ሠራተኞች ለኩባንያው ዕድገት ላበረከቱት አስተዋጽዖ እውቅና ለመስጠትና ለተሻለ ስራ ለማትጋት በማሰብ የ1 ወር ደመወዝ ቦነስ እና ተጨማሪ ለ14 ሰራተኞች የ14 ቤቶች ስጦታ ማበርከታቸውን አስታውቀዋል።
በኦቪድ ገላን ጉራ ከተማ ፕሮጀክት እየተገነቡ ከሚገኙትና በዚህ ዓመት ከሚጠናቀቁት 100 ብሎኮች መካከል 7 ስቱዲዮ፣ 4 ባለ አንድ መኝታ፣ 2 ባለ ሁለት መኝታ እና 1 ባለ ሶስት መኝታ በድምሩ 14 መኖሪያ ቤቶችን በስጦታ ማበርከታቸውን አቶ ዮናስ የገለጹ ሲሆን፣ ተሸላሚዎቹ በመጪው 2020 ዓ.ም ቤቶቻቸውን እንደሚረከቡም አረጋግጠዋል።
ኩባንያው የሦስተኛው ምዕራፍ ዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ጉዞውን በጀመረበት ወቅት ላይ የዕድገቱ መሠረት የሆኑትን የሠራተኞችን ተሳትፎ ቀን ማክበሩ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።
መርከበኞች አቅጣጫን ለመለየት እንደሚጠቀሙበት ኮከብ ሁሉ፣ ኦቪድም የቀጣይ ዓመታት አቅጣጫውን የሚጠቁም “ኖርዝ ስታር” የተሰኘ አዲስ ስትራቴጂ መቅረጹን የጠቆሙት አቶ ዮናስ፤ ስትራቴጂው ኩባንያውን ወደላቀ ስኬት ለመምራት የተነደፈ መሆኑን ገልጸዋል።
የኩባንያው ቦርድ ተወካይ እና የአንትራ ቢዝነስ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አንተነህ ተገኝ፤ ስትራቴጂውን በይፋ ያስተዋወቁ ሲሆን፤ የትራንስፎርሜሽኑን አስፈላጊነት፣ ዓላማዎች እና የትኩረት አቅጣጫዎች እንዲሁም በቀጣይ 5 ዓመታት የሚተገበሩ የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ዋና ዋና ግቦችንና የአሰራር መዋቅሮችን በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ስትራቴጂው በአግባቡ ወደ ተግባር እንዲቀየር እያንዳንዱ ሰራተኛና አመራር በየዕለቱ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በትጋት መወጣት እንደሚኖርበትም አሳስበዋል።
በመርሃ ግብሩ የኦቪድ ሆልዲንግስ እና የኮንስትራክሽን፣ የሪል እስቴት እንዲሁም የቴክኖሎጂና ማኑፋክቸሪንግ የንግድ ክፍሎች የ2019 ዓ.ም. አመታዊ ዕቅዶች በየዘርፍ የስራ ኃላፊዎች ቀርበዋል።
ሠራተኞች በበኩላቸው በትራንስፎርሜሽኑ፣ በቀረቡ ዕቅዶች እና በተለያዩ ተቋማዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን ያቀረቡ ሲሆን፣ የኩባንያው አመራሮችም ተገቢውን ምላሽ ሰጥተዋል፤ ሰፊ ውይይትም ተደርጓል።
ምንጭ፦ ኦቪድ ሆልዲንግስ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሚዩኒኬሽን


















