የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽንና ዓለም አቀፉ የሪፖርታጅ ፕሮፐርቲ (Reportage Properties) ጋር በጋራ ለመስራትና በዘላቂ ጥቅም ላይ ያተኮረ የልማት ሥራ ለማከናወን የሚያስችል ስትራቴጂያዊ ስምምነት ተፈራረሙ።
በስምምነቱ የፊርማ ሥነ-ሥርዓት ላይ የመከላከያ ፋይናንስ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ በተገኙበት የተካሄደ ሲሆን፣ ስምምነቱ ለሀገራዊ ዕድገት፣ ለዘላቂ ልማትና ለሠራዊቱ ተጠቃሚነት የሚኖረው ሚና የጎላ መሆኑን ገልጸው፤ የሁለቱ ተቋማት ትብብር ከግንባታ ባለፈ ለሀገሪቱ የከተማ ልማት፣ ለሥራ ፈጠራና ለቴክኖሎጂ ሽግግር አዲስ ዕድሎችን የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሜጀር ጀነራል ደረጀ መገርሳ በመግለጫው ላይ እንደገለፁት፣ በፕሮጀክቱ ከተማዋን የሚመጥን ዘመናዊ ግንባታ እንደሚካሄድና ይህም የሠራዊቱን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ዋና ዓላማው መሆኑን ገልጸዋል።
የሪፖርታጅ ፕሮፐርቲስ ዋና ሰብሳቢ ሚስተር አሪፍ አልኩሪ በበኩላቸው፣ ድርጅታቸው ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ በመስራቱ ደስታቸውን ገልጸው፤ የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አቅም፣ ፈጣን ዕድገት፣ አስተማማኝ ፀጥታ፣ እንግዳ ተቀባይነት እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት እና የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ መዲና መሆኗ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንዳደረጋት ገልጸዋል።
የሪፖርታጅ ፕሮፐርቲስ የኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሀናን አህመድ-ኑር በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ በ23 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ላይ የሚገነቡ ሁለት ግዙፍ እና ዘመናዊ ታወሮችን የሚያካትት መሆኑን ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ ውስጥ 1,083 የተለያዩ ደረጃ ያላቸው የመኖሪያ ቤቶች፣ የመዝናኛና የንግድ ቦታዎች፣ የመዋኛ ገንዳና ሌሎች ሙሉ ፋሲሊቲዎች እንደሚካተቱበት አስረድተዋል።
ፕሮጀክቱን በታቀደለት ጊዜ ለማጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሰሩ የገለጹት ወይዘሮ ሀናን፣ በፕሮጀክቱ ሂደት ከፍተኛ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂና የልምድ ሽግግር የሚገኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ተጨማሪ ስለ ሪፖርታጅ ፕሮፐርቲስ (Reportage Properties)
እ.ኤ.አ. በ2014 በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ (አቡ ዳቢ) የተመሠረተው ሪፖርታጅ ፕሮፐርቲስ፣ በግል ባለቤትነት የተያዘና በፍጥነት በማደግ ላይ ያለ ዓለም አቀፍ የሪል እስቴት አልሚ ኩባንያ ነው።
ኩባንያው በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ (አቡ ዳቢ፣ ዱባይ፣ ሻርጃ)፣ ግብፅ፣ ቱርክ፣ ሞሮኮ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ቤላሩስ እና ሩሲያ ጨምሮ ከ28 በላይ ሀገራት (8ቱ በአፍሪካ) የልማት ፕሮጀክቶችን በማንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። ሪፖርታጅ ፕሮፐርቲስ ዘመናዊና ማራኪ ዲዛይን ያላቸውን የመኖሪያ ታወሮች፣ ታውን ሃውሶችን (Townhouses) እና ሎፍቶችን (Lofts) በተመጣጠነ ዋጋ በማቅረብ የሚታወቅ ሲሆን፣ በዱባይ የሚገኘው Verdana እና Rukan፣ በአቡ ዳቢ የሚገኙት Masdar City እና Yas Island፣ እንዲሁም በካይሮ ግብፅ የሚገኘው Montenapoleone (ከ5,500 በላይ መኖሪያዎች ያሉት) ከሚገነቧቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል ተጠቀሾች ናቸው።
ምንጭ: የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት፣ ቤተኛ ሚዲያ


















