አንጋፋውና ተወዳጁ ጋዜጠኛ ደረጀ ሀይሌ የጃምቦ ሪል ስቴት ብራንድ አምባሳደር ሆኖ ስምምነት የፈጸመው ዛሬ ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም በሒልተን ሆቴል በተካሄደ ስነስርአት ነው።
ይህንን የብራንድ አምባሳደርነት የፊርማ ስነስርአት ከጋዜጠኛ ደረጀ ሀይሌ ጋር በመፈራረም ያበሰሩት አቶ ደበበ ሰይፉ የጃምቦ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ናቸው። በፊርማ ስነስርአቱ ላይ መልእክት ያስተላለፉት ዋና ስራ አስፈጻሚው ከተከበረው እና ተወዳጁ ጋዜጠኛ ጋር የአምባሳደርነት ምርጫ ያደረጉት በብዙ መስፈርቶች ሲሆን ጃምቦ ካለው አላማ እና እንቅስቃሴ ጋር ተመሳሳይ እና ትክክለኛ አላማ ያለው መሆኑን ጠቅሰው ጋዜጠኛ ደረጀም ትክክለኛ ምርጫችን ነው ብለዋል። አቶ ደበበ አያይዘውም ጋዜጠኛ ደረጀ ሀይሌ በቅርቡ በሰሜን አሜሪካን የኢትዮጵያውያን የስፖርት ፌስቲቫል ላይ ጃምቦ ሪል ስቴትን ወክሎ የመጀመሪያውን የስራ እንቅስቃሴ ይጀምራል ብለዋል።

በብራንድ አምባሳደርነት ፊርማ ስነስርአት ላይ ጃምቦ ሪል ስቴት የተቀላቀለው ጋዜጠኛ ደረጀ ሀይሌ ለዚህ ክብር ለመብቃት ትልቁን ድርሻ የተወጡትን ወዳጅ፣ጓደኞችን እንዲሁም ጃምቦ ሪል ስቴት ይህንን እድል ስለሰጠው ምስጋና አቅርቧል። ግሩፑ ልሰራቸው ያሰብኳቸውን የጽህፈት ስራዎች ተረጋግቼ እንድሰራ እድሉን ስለሰጠኝ አመሰግናለሁ ብሏል። “የምችለው ጋዜጠኝነትን ብቻ ነው። ጋዜጠኝነት አልከፈለኝም ብዬ አማርሬ ግን አላውቅም። ሬዲዮ ማይክራፎን ፊት ለፊት ስቀመጥ ነብሴ ሀሴት ታደርጋለች። ሙያው ምንም ገንዘብ ባያስገኝም ወዳችሁት ስሩ። በቅርቡ “ጃምቦ የኔም ነው በሚል ማስታወቂያ እመጣለሁ።”ብሏል።
ጋዜጠኛ ደረጀ ሀይሌ ጃምቦ ሪል ስቴት ካስገነባው የሪል ስቴት ግንባታ በአፍሪካ ህብረት ከሚገኘው ሳይት ባለ ሁለት መኝታ መኖሪያ ቤት የተበረከተለት ሲሆን በብራንድ አምባሳደርነት አብሮ ለመስራት የሶስት አመታት ውል ፈጽመዋል። ጃምቦ ሪል ስቴት ከሀያ ዘጠኝ አመታት በፊት በወንድማማቾቹ አቶ ደበበ ሰይፉ እና አቶ ወንድይራድ ሰይፉ አማካኝነት ጃምቦ ኮንስትራክሽን በሚል ስያሜ የተቋቋመ ሲሆን በኮንስትራክሽን ዘርፍ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ከ100 በላይ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ እስረክቧል። በሪል ስቴት ዘርፍም በ16 ፕሮጀክቶች 700 ቤቶችን ገንብቶ ለደንበኞች ያስረከበ ሲሆን በአሁኑ ጊዜም ከ1000 በላይ ቤቶችን ግንባታ እያከናወነ እንደሆነ የጃምቦ ሪል ስቴት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም ጌታቸው ገልጸዋል።
ምንጭ፡ Jambo Real Estate


















