ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ በዛሬው እለት በከፍተኛ ፍርድ ቤት የፍትሃ ብሄር ምድብ ችሎት፣ የቢጂአይ ኢትዮጵያ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችና የባንክ አካውንቶች እንዳይንቀሳቀሱና ገንዘብ እንዳይሰወርብኝ በሚል ባቀረበው የእግድ ጥያቄ መሰረት፣ ፍርድ ቤቱ አቤቱታውን ተቀብሎ የባንክ አካውንትና የማይንቀሳቀሱ የቢጂአይ ኢትዮጵያ ንብረቶች እንዳይሸጡና እንዳይለወጡ እግድ መጣሉን ምንጮች ጠቁመዋል።
መዝገቡ ለችሎት ሊቀርብ የቻለው አመልካች ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ፣ በጠበቆቹ አማካኝነት ባለፈው ረቡዕ የካቲት 27 ቀን 2016 ዓ.ም በተፃፈ አቤቱታ፣ የክስ ዝግጅት አጠናቅቆ የ1, 519,000000 (አንድ ቢሊዮን አምስት መቶ አስራ ዘጠኝ ሚሊዮን) ብር ክስ እስከማቀርብ ድረስ ተጠሪ ቢጂአይ ኢትዮጵያ፣ ጥሬ ገንዘብ እንዳይሰውርብኝ እንዲሁም የማይንቀሳቀስ ንብረቱ እንዳይሸጥብኝ አስቸኳይ እግድ ይሰጥልን የሚል አቤቱታ ስላቀረበ መሆኑን ምንጮች ገልፀዋል።
የአቤቱታው ይዘትም በአመልካችና በተጠሪ መካከል በ08/10/2015 በተፈረመ የሽያጭ ውል የተጠሪን ዋና መስሪያ ቤትና ተጨማሪ ይዞታውን በአጠቃላይ ስፋቱ 29 ሺህ 896.51 ካ .ሜ የሆነ ቦታ ላይ ያረፈ ንብረት በ5 ቢሊዮን ብር፣ ተጨማሪ እሴት ታክስን ሳይጨምር፣ ለመግዛት ተዋውለው እንደነበርና ግዢው የተፈፀመው በሒደት በሚደረግ የክፍያ ስርዓት እንደመሆኑ አመልካች የመጀመሪያውን 20 በመቶ ማለትም 1 ቢሊዮን 150 ሺህ ከእነ ተጨማሪ እሴት ታክሱ መክፈሉን አመልካች በአቤቱታው ጠቅሷል።
ተጠሪ በውሉ እንደተመለከተው፣ ሁለተኛ ዙር ክፍያ የሚከፈለው በቅድሚያ የካፒታል ትርፍ ታክስና ከእዳና እገዳ ነፃ ስለመሆኑ ማስረጃ ሲያቀርብ በመሆኑ፣ ይህን እንዲፈፅም ቢጠየቅም፣ ለማድረግ ካለመፈለጉም ባሻገር ያለምንም በቂና አሳማኝ ምክንያት በመካከላችን ያለውን ውል አቋርጫለሁ ክፍያውንም አልመልስም ሲል፣ የህዝብና የደሃ ማህበረሰብን ገንዘብ ከህግና ከስርዓት ውጪ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ውሉን አቋርጧል፤ ገንዘቡንም አልመልስም ሲል በደብዳቤ አሳውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ መሬቱን ለሶስተኛ ወገን እሸጣለሁ ሲል እንቅስቃሴ ስለመጀመሩ መረጃ እንደደረሰው ፐርፐዝ ብላክ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት፣ የፍትሃ ብሄር ምድብ ችሎት አቤቱታ ማቅረቡም ተሰምቷል።
በመሆኑም ተጠሪ የውል ግድዴታውን አሟልቶ ባለመፈፀሙ የተነሳ አመልካች የመጀመሪያ ደረጃ 20 በመቶ ከፈፀመበት ጊዜ ጀምሮ ይህን አቤቱታ እስካቀረበበት የካቲት 27 ቀን 2016 ዓም ድረስ ገንዘባችንን ሲጠቀምበት ስለነበር፣ ህጋዊ ወለድ 9 በመቶ ታስቦ፣ የብር 69 ሚሊዮን ለልዩ ልዩ ወጪ የሚከፈል ክፍያ ብር 250 ሚሊዮን፣ ለዳኝነት የሚከፈል ብር 50 ሚሊዮን፣ በድምሩ የ1 ቢሊዮን 519 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ክርክር ስላለን፣ ተጠሪ ወደፊት ፍርድ እንዳይፈፀምበት ንብረት የማሸሽና የመሰወር ስራ ሊሰራ እንደሚችል ከፍተኛ ጥርጣሬ አለን፤ ይህም ከሆነ የማይተካ ኪሳራና ውድቀት ያደርስብኛልና ጊዜ ወስጄ ክስ እስክመሰርት ድረስ በአስቸኳይ የእግድ ትዕዛዝ ይሰጥልኝ ሲል አቤቱታውን ለከፍተኛው ፍርድ ቤት የፍትሃ ብሔር ምድብ ችሎት ማቅረቡን ምንጮች ጨምረው ገልፀዋል።
ፍርድ ቤቱም፣ ይህን አቤቱታ ካጤነ በኋ፣ላ አንደኛ ተጠሪ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ስር የሚተዳደሩ ሁሉም ባንኮች ውስጥ ባለው የባንክ ሒሳብ አመልካች የጠቀሰው የገንዘብ መጠን፤ ሁለተኛ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 የቤት ቁጥር 017 (የካርታ ቁጥሩ ተጠቅሷል) የሆኑ ይዞታዎች በአጠቃላይ ስፋቱ 29 ሺህ 896.51 ካ.ሜ የሆነው ይዞታ ሳይሸጥ ሳይለወጥ ወይም በማንኛውም ሁኔታ ለሶስተኛ ወገን ሳይተላለፍ ታግዶ እንዲቆይ የእግድ ትዕዛዝ መስጠቱም ተሰምቷል።


















