የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሕዝብ መዝናኛ ኮርፓሬሽን ከሚያስተዳድራቸው 10 ፓርኮች መካከል 5ቱ በንጉሱ እና በደርግ ጊዜ የተሰሩና ከስታንዳርድ በታች በመሆናቸው ለማልማት / ደረጃቸውን ለማሻሻል ታቅዶ ለ3ቱ ዲዛይን ተሰርቶ አንዱን ማልማት መጀመሩን አስታውቋል።
ኮርፓሬሽኑ ይህንን ያለው ባለፈው ቅዳሜ በሰጠው መግለጫ ሲሆን የሚታደሱትም ፦
- ኩባ ፓርክ፣
- ሐምሌ 19፣
- ብሔረ ፅጌ፣
- ኮሪያ ዘማቾች መታሰቢያ፣
- አዲስ ዙ (ፒኮክ) ፓርኮች መሆናቸውን ገልጿል።
ለማልማት ምን ያህል በጀት ያስፈልጋል ? ተብሎ ጥያቄ የቀረበለት ኮርፖሬሽኑ ፥ “ Estimation በጀቱ ትልቅ ነው። የኮንስትራክሽን በጀቶቹ ቀላል አይደሉም ” ብሏል።
“ አሁን አዲሱ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ የሚፈጅ ፕሮጀክት ነው የተጠናው። በተግባር ሲገባ ስንት ይሆናል ? የሚለው በወቅቱ የምናሳውቅ ይሆናል። ኮሪያ ፓርክ ላይም እየሰራን ያለነው ከ100 ሚሊዮን ብር ባለፈ ወጪ ያለው ነው ” ሲልም አክሏል።
‘ ስድስት ኪሎ ‘ ያለው ፓርክ ጥንታዊ እና ታሪካዊ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በመሆኑ ሲታደስ የታሪክ ትዝታዎቹ አይጠፉም ወይ ? ተብሎ ለቀረበው ጥያቄም፣ “ 6 ኪሎም ሆነ ሌሎቹን በፊት ያለውን መሠረታዊ ነገር እንዲለቅ አይፈለግም ” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
“ የፓርኮች ልማት ጤናማ የሆነ ማህበረሰብ እንዲኖር የማድረግ እድል ይኖረዋል። ስለዚህ በእኛ በኩል ከማንኛውም ልማት በላይ ትኩረት ሰጥተን የምንሰራው፣ ሕዝብንና ተፈጥሮን የማገናኘት ጉዳይ ነው የፓርክ ጉዳይ ” ብሏል ኮርፖሬሽኑ።
“ የፓርክ ልማት ለአዲስ አበባ የህልውና ጉዳይ ነው። ትርፍ ስራ አይደለም ፤ የ Prioritization ስራም አይደለም ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው ፤ አለበለዚያ ከተማው በአንድ ጀንበር የመጥፋት እድል ነበረው ” ሲል ገልጿል።
“ በዛ መልክ የማንሰራ ከሆነ የከተማው ህልውና አደጋ ላይ ነው ያለው። የማህበረሰቡ አኗኗር ለበሽታ የመጋለጥ እድሉ በጣም ከፍተኛ ነው። ፓርክ መስራት ማለት ለሕዝቡ ኦክስጂን መስጠት ነው ” ነው ያለው።
በቀጣይም በኮሪደር ልማት ስራ በርካታ ፓርኮች እና መዝናኛ ቦታዎች እንደሚሰሩ ያመለከተው ኮርፖሬሽኑ እነዚህንም በማካተት ” የህዝቡን የመዝናኛ እና ንጹህ ቦታ የመኖር ፍላጎት እንዲሟላ እንሰራለን ” ብሏል።

















