በአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን የለሚኩራ ቅ/ጽ/ቤት የመንገድ ደህንነት ግንዛቤና ደንብ ማስከበር ዳይሬክቶሬት የትራፊክ ቁጥጥር ቡድን በመንገድ ላይ አፈርና ጭቃ እያንጠባጠቡ አስፓልት ያበላሹ አሽከርካሪዎችን በልዩ ኦፕሬሽን እንዲቀጡ አድርጓል፡፡
በተለይም በ90 ቀናት የተግባር ክንውን ወቅት የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎች በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ አፈርና ጭቃ ከጎማ ላይ ሳያፀዱ ወደ መንገድ እንዳይወጡ እንዲሁም ከመጠን በላይ ትርፍ አፈርና ቆሻሻ እንዳይጭኑ ተገቢውን ቁጥጥር እዲደረግ ለቁጥጥር ሰራተኞች አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡
በአቅጣጫ መሰረት በትናንትናው እለት በክፍለከተማው በፊጋና ጎሮ ሳይቶች በልዩ የቁጥጥር ኦፕሬሽን በተካሄደ ቁጥጥር አብዛኛው አሽከርካሪዎች ከሚጭኑበት ቦታ የተሸከርካሪያቸውን ጎማ እንዲያጸዱ ተደርጓል፡፡
በአጫጫን ጥንቃቄ ጉድለት እና ከተሸከርካሪዎች ጎማ ላይ ጭቃ ሳያጸዱ አስፓልት መንገድን ያበላሹ 9 አሽከርካሪዎች በደንብ 395/2009 በእርከን 1/14 መሰረት በገንዘብ መቀጣታቸውን የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የመንገድ ደህንነት ግንዛቤና ደንብ ማስከበር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መሀመድ በላይ ገልፀዋል።

















