በሙስና እንዲሁም በሌሎች ህገ ወጥ ተግባራት አማካኝነት የሚገኝ ገንዘብን ህጋዊ ለማስመሰል በሚደረግ ሂደት ውስጥ የትኞቹ ዘርፎች ይበልጥ ተጋላጭ ሆነዋል ሲል መናኸሪያ ሬዲዮ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎትን የጠየቀ ሲሆን፤ በዚህም የሪል እስቴት እንዲሁም የተሽከርካሪ ንግድ ከፍተኛ ተጋላጭ ዘርፎች መሆናቸውን አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡
ለሪል እስቴት ቤቶች እንዲሁም ለተሽከርካሪዎች ግዢ የሚወጣው ገንዘብ ከፍተኛ መሆኑ ለህገ ወጥ እንቅስቃሴው አጋላጭ ሆኗል ያሉት የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ፤ ይህንን መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ሥራዎች እተከናወኑ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡
ሙስና እንዲሁም ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በህገወጥ መንገድ ገንዘብ ከሚገኝባቸው ተግባራት መካከል ግንባር ቀደም መሆናቸውን አክለው የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መዋእለ ንዋይ በማፍሰስ ገንዘቡን ህጋዊ ለማስመሰል የሚደረጉ ጥረቶችን በጥናት ላይ ተደግፈው የመከላከከል ሥራዎችን እየተከናወኑ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
በተለይም በሪል እስቴት ዘርፍ ያሉ የህግ ክፍተቶችን መሙላት ሲቻል ህገ ወጥ እንቅስቃሴውን ለመከላከል አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጠር ነው አቶ ሙሉቀን የጠቆሙት፡፡
ምንጭ፦ መናኸሪያ ሬዲዮ


















