ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር በልደታ ክፍለ ከተማ ሁለት ባለ ዘጠኝ ፎቅ የመኖሪያ ቤት ህንጻዎችን ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ። መኖሪያ ቤቶቹ ለልማት ተነሺዎች የሚሰጡ እንደሆኑ ተጠቁሟል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እና የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ በልደታ ክፍለ ከተማ ሁለቱ አካላት በመተባበር ለልማት ተነሺዎች የሚያስገነቡት ባለ ዘጠኝ ፎቅ የመኖሪያ ቤት ህንጻ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠላችው ሁለት ህንጻዎች በአጠቃላይ 180 መኖሪያ ቤቶችን የሚይዙ ሲሆን ከወራት በፊት ግንባታችው የተጀመሩና በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙት ሁለት ሌሎች ባለ 8 ፎቅ ሕንጻዎች ደግሞ 140 መኖሪያዎችን ይይዛሉ።
ይህ ማለት በአሁኑ ሰዓት ሚድሮክ እና ከተማ አስተዳደሩ 320 መኖሪያ ቤቶችን አስገንብተው ለልማት ተነሺዎቹ ለማስረከብ እየሰሩ ነው።
ህንጻዎቹ በዋነኛነት ከዓድዋ ድል መታሰቢያ ዙሪያ እና ከልደታ ክፍለ ከተማ በተለያዩ የልማት ስራዎች ለሚነሱ ነዋሪዎች የሚዘጋጁ ናቸው።

ከተማ መታደስ እና መልማት አለበት ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተማዋን ስናለማ ግን ነዋሪውን ወደ ዳር በማውጣት ሳይሆን በመሀል ከተማ ለኑሮ ተስማሚ በሆነ ስፍራ ምቹ የሆኑ ቤቶችን ገንብቶ ለነዋሪዎች በማቅረብ ነው ብለዋል።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የከተማ አስተዳደሩ የነዋሪዎችን ህይወት ለማሻሻል በሚያካሂዳቸው የሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች ለሚያደርገው ያልተቋረጠ ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ቤቶቹ በሶስት ወራት ውስጥ ተገንብተው እንደሚጠናቀቁም አስታውቀዋል።
ምንጭ፦ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ

















