ኦቪድ ሪል እስቴት በአዋሬ አካባቢ በኦቪድ ኮንስትራክሽን ያስገነባውንና ለአገሪቱ አዲስ የሆነ የግንባታ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ እንደዋለበት የተነገረለትን ባለ 11 ወለል የመኖሪያ ቤቶች ህንጻ በማስመረቅ ለደንበኞቹ ያስረከረ ሲሆን፣ ህንጻው በአጠቃላይ 50 መኖሪያ ቤቶችን የያዘ ነው፡፡
የፕሮጀክት ማናጀሩ ኢንጂነር አቤል ኢሳያስ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት 426 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ ያረፈው ህንጻው ከምድር በታች፣ በምድር ቤት እና በአንደኛ ወለል በቂ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ያለው ሲሆን፣ ዘመናዊ አሳንሰሮችም ተገጥመውለታል፡፡
ህንጻውን መርቀው የከፈቱት የኦቪድ ሪል እስቴት ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ሙሉቀን ምትኩ ኦቪድ ሪል እስቴት በዘመናዊ የህንጻ ግንባታ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ቤቶችን በጥራትና በፍጥነት እየገነባ በተመጣጣኝ ዋጋ ለዜጎች ለማዳረስ የሰነቀውን ህልም ለማሳካት በትጋት እየሰራ እንደሚገኝ በመግለጽ፣ ይህ ፕሮጀክትም የዚህ ስኬት ጅማሬ ማሳያ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የኦቪድ ሆልዲንግ እህት ኩባንያዎች የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች፣ ቤት ገዢዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በተካሄደው የምረቃ ስነስርዓት ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኦቪድ ሪል እስቴት ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ሙሉቀን፣ ኩባንያው አዳዲስ የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን በማስመጣት በአገሪቱ የሪል እስቴት ዘርፍ ተጨባጭ ለውጦችንና ውጤቶችን ለማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በማህበራዊ ሃላፊነት ረገድ በርካታ ተጠቃሽ ስራዎችን በማከናወን የሚታወቀው ኦቪድ ሪል እስቴት በዚህ ፕሮጀክትም ይህን በተግባር ማረጋገጡንም አስታውሰዋል፡፡
በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙና የፕሮጀክቱ ቤት ገዢዎች ኦቪድ ሪል እስቴት በገባው ቃል ኪዳንና የግዢ ውል ስምምነት መሰረት በወቅቱ ግንባታውን አጠናቅቆ ቤታቸውን ስላስረከባቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው በመግለጽ፣ የኩባንያውን አመራሮችና ሰራተኞች ከልባቸው አመስግነዋል፡፡
ኦቪድ ሪል እስቴት ከወራት በፊትም በአራት ኪሎ ጥይት ቤት ኪንግስ ታወርስ ሳይት የመጀመሪያ ምዕራፍ ያስገነባቸውን 249 ቤቶች ያካተቱ ሶስት ብሎኮች በማስመረቅ፣ 990 የመኖሪያ ቤቶችንና የንግድ ተቋማትን ያካተተውንና ጂ ፕላስ 13 ወለሎች ያላቸው 17 ህንጻዎችን የያዘውን የሁለተኛ ምዕራፍ የፕሮጀክት ግንባታ ስራና ሽያጭ በይፋ ማስጀመሩ ይታወሳል፡፡
ምንጭ፡ ኦቪድ ሆልዲንግ ኮሙኑኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት


















