አቡቀለምሲስ የሪል እስቴት ማሰልጠኛ ተቋም ከኢትዮ አልያንስ አድቮኬትስ ጋር ለቤት ገዥዎች ያሰናዳውን ልዩ ሥልጠና አካኼደ።
አቡቀለምሲስ የሪል እስቴት ማሰልጠኛ ተቋም ከኢትዮ አሊያንስ አድቮኬትስ ጋር በመተባበር ለቤት ገዥዎች የተዘጋጀ ልዩ ሥልጠና በሳፋየር አዲስ ሆቴል ዛሬ የካቲት 16/2016 ዓ.ም አካኼደ።
ኢንጅነር ደሳለኝ ከበደ የአቡቀለምሲስ ሪል እስቴት መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ስለሥልጠናው በሰጡት መግለጫ የሪል እስቴት ቤቶች ግብይት ሰፊና ብዙ አማራጮች ያሉት ከመኾኑ አንፃር በሽያጭ ወቅት አንዳንድ ሁኔታዎችን ካለማወቅ ገዥዎች ለጉዳት የሚዳረጉበት ሁኔታ ለመቀነስ እና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ግብይት ለማከናወን ታስቦ ሥልጠናው መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።
ለቤት ገዥዎች ሥልጠና ለእኛ ሀገር አዲስ ቢኾንም በውጭ ሀገራት የተለመደ መኾኑን ያስታወሱት ኢንጅነር ደሳለኝ ይኸን ጅምር አጠናክሮ ለመቀጠል ድርጅታቸው መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

ኢንጅነር ደሳለኝ አያይዘውም የሪል እስቴት የሽያጭ ሠራተኞች ወይንም ወኪሎች የሪል እስቴት አልሚውን ወይንም ሻጩን የሚወክሉ ናቸው፤ ገዥው ቤት የሚገዛው ምናልባት በሕይወት ዘመኑ አንድ ጊዜ ሊሆን ስለሚችል የራሱን ጥቅም የሚያስጠብቅ ወኪል ያስፈልገዋል ብለዋል።
ድርጅታቸው የሪል እስቴት ቤት የሚገዙ ሰዎችን በተናጠል ወይንም በቡድን የማማከር ሥራ ጭምር እንደሚያከናውን የጠቀሱት ኢንጅነር ደሳለኝ ምናልባትም በሕይወት ዘመን አንድ ጊዜ ለቤት ግዥ የሚውል ከፍተኛ ገንዘብ ለውስብስብ ችግሮች እንዳይዳረግ ገዥዎች አስቀድመው ሊጠነቀቁ እንደሚገባ መክረዋል።
አቶ ቃለእግዚአብሔር ጎሳዬ ከኢትዮ አሊያንስ አድቮኬትስ የሪል እስቴት ቤቶች ግብይትን አስመልክተው በሥልጠናው ላይ ካነሷቸው ነጥቦች መካከል በግዥ ወቅት በውልና ማስረጃ የተረጋገጠ የውል ሰነድ እንደሚያስፈልግ፣ በውሉ ውስጥ ስለሚገዙት ቤት ዝርዝር መረጃ መያዙን፣ ስለክፍያ ጊዜ፣ ስለቤት ርክክብ ጊዜና የመሣሠሉት መካተታቸውን በሕግ ባለሙያ ታግዘው ቢያከናውኑ በኋላ ከሚከሰት አለመግባባት እንደሚጠብቅ፣ አለመግባባቱ ቢከሰትም በሕግ ተከራክሮ ለማሸነፍ ጠቃሚ መሆኑን አሳስበዋል።
አቡቀለምሲስ የሪሌስቴት ማሰልጠኛ ተቋም እስካሁን በ24 ዙሮች የቤት ሽያጭ ባለሙያዎችን ለሪል እስቴት ኢንቨስትመንት ውስጥ ተሰማርተው ላሉና አዳዲስ አልሚዎች ስልጠናና የአዋጭነት ጥናትን የሰጠ ሲሆን ፣ በሪል እስቴት ኩባንያዎች ጥያቄ መሠረት በዘርፉ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ሲሰጥ መቆየቱን ኢንጅነር ደሳለኝ ከበደ አስታውሰዋል።
በቀጣይም ለቤት ገዢዎች የሚሰጠው ስልጠና በግለሰብ እና በቡድን ለተደራጁ ገዢዎች በሚታቀርቡት ጥያቄ መሰረት የሚሰጥ ሲሆን ቤት ገዢዎችንም በግብይት ሂደት ውስጥ ለማገዝ ተቋማቸው ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።


















