ጊፍት ሪል እስቴት በመንግስትና የግል አጋርነት ልማት ፕሮጀክት 12 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ከተያዘው ስምምነት መካከል የሁለተኛው ምዕራፍ ፕሮጀክት ግንባታ ማስጀመሪያና ማስተዋወቂያ እንዲሁም ሶስተኛው “መኖር በጊፍት መንደር ” የሽያጭ ኤክስፖ መርሃ ግብር በዛሬው እለት ተጀመረ።
ለረጅም ዓመታት በኢትዮጵያ የሪል እስቴት ዘርፍ ግንባር ቀደም ተወዳዳሪ የሆነው ጊፍት ሪል እስቴት “መኖር በጊፍት መንደር” በሚል መሪ ቃል ሶስተኛው የሽያጭ ኤክስፖ ከዛሬ ግንቦት 19 እስከ ግንቦት 24 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚያካሄድ አሳወቀ።
የጊፍት ሪልስቴት የሽያጭ እና ማርኬቲንግ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ብርቁ ይርጋ እንደገለጹት ጊፍት ሪል እስቴት ለገዢዎች እስከ 30 በመቶ የሚደርስ የአጭር ጊዜ ቅናሽ ያቀረበ ሲሆን ከ9 በመቶ እስከ 25 በመቶ ቅድመ ክፍያ በመክፈል የቤቶቹ ባለቤት መሆን እንደሚቻል እና የዚህን ታላቅ ቅናሽ ተጠቃሚ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል።
ጊፍት ሪል እስቴት አዳዲስ ሦስት መንደሮችን ጨርሶ ለቤት ባለቤቶች ካስረከበ በኋላ በአራተኛው የጊፍት ሜትሮፖሊታን መንደር በለገሃር 4 ሺህ ቤቶችን በመገንባት ላይ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም በሁለተኛና ሶስተኛ ዙሮች የሚገነቡ 8 ሺህ የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶችን እንዲሁም በ6 ኪሎ፣ በቦሌ መድሃኒዓለም፣ በፊጋ፣ በ22 ማዞሪያ፣ በተክለሃይማኖት፣ በሲኤምሲ እና በሌሎች አካባቢዎች 4 ሺህ ቤቶችን በአጠቃላይ ከ16 ሺህ በላይ ቤቶችን ለሽያጭ አቅርቧል።
እነዚህ ግንባታዎች በሚከናወኑባቸው መንደሮች ትምህርት ቤቶች፣ የህክምና ተቋማት፣ የገበያ ማዕከላት፣ የሀይማኖት ተቋማት ፣ የመዝናኛ ስፍራዎች እና የመኪና ማቆሚያዎች እንደሚኖሩ ተገልጿል።
ጊፍት ሪል እስቴት እስካሁን በ165 ሺህ ካሬሜትር ላይ በሲኤምሲ እና ፈረስ ቤት ሦስት ትላልቅ መንደሮችን ገንብቶ ለማኅበረሰቡ ማስረከብ መቻሉ የተመላከተ ሲሆን ዓለም የደረሰበትን የግንባታ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ዘመናዊ እና ቅንጡ የመኖሪያና የንግድ አፓርትማ መንደሮችን እየገነባ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
ምንጭ፡ ጌጡ ተመስገን


















